
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)”ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ መልዕክት ክልል አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ እና ብክለትን መከላከል ዘመቻ የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው። በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ለማስጀመር በተዘጋጀው የንቅናቄ መድረክ ላይ የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የፌዴራል፣ የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እንዳሉት የአየር ንብረት ለውጥ በሰዎች እና በተፈጥሮ መካከል የተዛባ ግንኙነት ምክንያት የሚፈጠር ችግር ነው። የሰው ልጅ ተፈጥሮ ያደለችውን ጸጋ በአግባቡ ባለመጠቀም በድርቅ፣ በረሃብ፣ በጎርፍ እና በመሳሰሉ ችግሮች የጤና መታወክ እየደረሰበት መኾኑን ገልጸዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ችግሩ የዓለማችን ስጋት እየኾነ መምጣቱን ገልጸዋል። የዓለም ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ፖሊሲዎችን ነድፈው እየሠሩ መኾኑን አንስተዋል። ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ፖሊሲ በማውጣት እየሠራች መኾኑን ገልጸዋል። ለዚህም የአረንጓዴ ልማት መርሐ ግብርን ባለፉት ዓመታት ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መኾኑን አንስተዋል። የአረንጓዴ ልማት ሥራው የአካባቢ ብክለትን ከመከላከል ባለፈ የገቢ ምንጭ እንዲኾን ትኩረት መደረጉን ነው ርእሰ መሥተዳደሩ የገለጹት።
አሁን ላይ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ እያስከተለ የሚገኘው ብክለት በየአካባቢው በዘፈቀደ የሚጣሉ ፕላስቲኮችን ዘወትር በማጽዳት አካባቢን ከብክለት ነጻ የማድረግ እና ሥነ ምህዳርን በዘላቂነት የመጠበቅ ሥራ የሁሉም ኅብረተሰብ ኀላፊነት ሊኾን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ብክለት እያስከተለ ያለውን አደጋ በዘላቂነት ለመከላከል እና የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት ለመጠበቅ በየደረጃው የሚገኘው አመራር እና ባለሙያ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በከተሞች የሚሰተዋለውን የፕላስቲክ ቆሻሻ ብክለትን የማስወገድ ብቻ ሳይኾን መልሶ የምንጠቀምበት ሁኔታ እንዲፈጠር ሁላችንም ልንሠራ ይገባል ብለዋል። የክልሉ የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ተስፋሁን ዓለምነህ እንዳሉት ደግሞ ብክለት የአካባቢን ሥነ ምህዳር ከመጉዳት ባለፈ ሕይወት ላላቸው አካላት ሞት መንስዔ እየኾነ ይገኛል።
ከብክለት ነጻ እና ለኑሮ ተስማሚ የኾነ አካባቢን ለመፍጠር በተለይም ከፕላስቲክ ቆሻሻ ነጻ የኾኑ ከተሞችን ለመፍጠር ባለሥልጣኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል። የአካባቢ ብክለትን መከላከል ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ባለመኾኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በእቅዳቸው አካተው ሊሠሩ እንደቢገባም ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!