
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተውን የእሳት አደጋ መቆጣጠር መቻሉን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል። ከሰሞኑ በፓርኩ ውስጥ የእሳት አደጋ ተከስቶ ነበር። የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ርብርብ እየተደረገ መኾኑን የሰሜን ጎንደር ዞን አሥተዳደር መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል።
የተከሰተው የእሳት አደጋ በተደረገው ርብርብ መቆጣጠር መቻሉን ነው የተገለጸው። ነገር ግን መልሶ ሊያገረሽ ስለሚችል መዘናጋት አይገባም ተብሏል። የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አበበ እምቢአለ የተከሰተውን የእሳት ቃጠሎ ለማስቆም ክትትል እየጠደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
የእሳት ቃጠሎውን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል በሰሜን ጎንደር ዞን ኮሚቴ ተቋቁሞ መሠራቱን ነው የገለጹት። የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማስተባበር በተሠራ ሥራ ቃጠሎው እየበረደ መኾኑንም ተናግረዋል። ነገር ግን በደንብ ካልጠፋ በነፋስ ምክንያት እንደገና ሊያገረሽ እንደሚችልም አመላክተዋል።
ከትናንት ጀምሮ የእሳት ቃጠሎው እየበረደ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው ፓርኩ ከፍተኛ ክትትል እና ቁጥጥር እንደሚያስፈልገውም ገልጸዋል። በተለይም በጃናሞራ ወረዳ በኩል የተከሰተው የእሳት ቃጠሎ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉንም አስታውቀዋል። በደባርቅ በኩል ያለው የእሳት ቃጠሎ ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ እንደነበር የተናገሩት ኀላፊው ባደረጉት ክትትል እሳቱን መቆጣጠር ተችሏል ነው ያሉት።
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪስት መዳረሻ እና ለበርካታ ወገኖች የሥራ እድል የፈጠረ መኾኑንም ተናግረዋል። ለበርካታ ወገኖች የሥራ እድል የፈጠረው ፓርክ ሊጠበቅ እንደሚገባውም አመላክተዋል። ፓርኩ የሚጠበቀው አካባቢው ሲጠበቅ መኾኑንም ገልጸዋል። የእሳት አደጋው መልሶ እንዳያገረሽ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። ቃጠሎውን በሚገባ መቆጣጠር ካልተቻለ ሁኔታዎች ሊቀየሩ ይችላሉ፣ ባለመዘናጋት መከታተል እና መቆጣጠር ይገባል ብለዋል።
እሳቱ የሚያገረሽ እና ከአቅም በላይ ከኾነ የፌዴራል መንግሥት እገዛ ተጨምሮበት መቆጣጠር ይገባል ነው ያሉት። ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የፓርኩን ደኅንነት መጠበቅ አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል። የባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የፓርኩ ደኅንነት እንዲጠበቅ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ይሠራል ነው ያሉት። በተለይም በሚያዚያ እና በግንቦት ወራት ክትትል እና ቁጥጥር ሊደረግለት ይገባል ብለዋል። ፓርኮችን መጠበቅ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተደረገ መኾኑንም አመላክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
