
ጎንደር: ሚያዚያ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የመሰረተ ልማት አማካሪ ደሴ አሰሜ እና የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች በከተማው እየተሠሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሀይ በ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጭ እየተገነቡ የሚገኙ ከ80 በላይ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል። መሰረተ ልማቶቹ ለሁለንተናዊ የልማት እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ወሳኝ በመኾናቸው ማኅበረሰቡ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የከተማ እና መሰረተ ልማት መምሪያ ዋና ሥራ አሥኪያጅ አንዱዓለም ሙሉ እየተሠሩ ያሉ የመንገድ እና የድልድይ ፕሮጀክቶችን ተከትሎ ሌሎች መሰረተ ልማቶችም እንደሚሟሉ ገልጸዋል። ለአብነትም የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የስልክ መሰረተ ልማቶች እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታዎች እንዲስፋፉ እድል እንደሚሰጥ አንስተዋል።
የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶቹን የጎበኙት የርእሰ መሥተዳድሩ የመሰረተ ልማት አማካሪ ደሴ አሰሜ ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ ከተማዋን በምጣኔ ሃብት እና በቱሪዝም እንቅስቃሴ ያሳድጓታል ብለዋል። አማካሪው የከተማ አሥተዳደሩ እየሠራቸው የሚገኙ ሥራዎች መልካም መኾናቸውን ገልጸው ከከተማው አቅም በላይ የኾኑ ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም ክልሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አገኘሁ አበባው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!