
ደባርቅ: ሚያዚያ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከሰሞኑ የእሳት ቃጠሎ ተከስቷል። የእሳት ቃጠሎውን ለማጥፋት ርብርብ እየተደረገ መኾኑን የሰሜን ጎንደር ዞን አስታውቋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ቢምረው ካሳ የቃጠሎው መጠን ይለያያል እንጂ በተደጋጋሚ ቃጠሎ እንደሚነሳ ተናግረዋል። በአካባቢው ከአርሶ አደሮች የሕገ ወጥ ከሰል ማክሰል ጋር በተያያዘ ቃጠሎ እንደሚነሳ ነው የገለጹት። በየዓመቱ ከመጋቢት እስከ ሰኔ ወር ድረስ የተለየ ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚደረግለትም ተናግረዋል።
አሁን ላይ የተፈጠረው የእሳት ቃጠሎም ከአሁን በፊት ሲከሰት እንደነበረው የተፈጠረ ሳይኾን እንዳልቀረ ነው ያመላከቱት። በፓርኩ ሚያዚያ 10/2016 ዓ.ም ምሽት ሦስት ሰዓት ጀምሮ የእሳት ቃጠሎ መነሳቱን ገልጸዋል። የእሳት ቃጠሎው እንደተፈጠረ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና የፓርኩ ሠራተኞች ለማጥፋት ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን አቶ ቢምረው ተናግረዋል።
በጣም ከፍተኛ ሥፍራ በመኾኑ ጠፋ ሲባል መልሶ በመቀጣጠል እንደሚሰፋም ገልጸዋል። ቃጠሎው እየሰፋ ሲሄድ በሰው ኃይል መቆጣጠር የሚቻለውን ለመቆጣጠር የሚያስችል ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ሥራ መግባታቸውንም አስታውቀዋል። የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ለማጥፋት መሠራቱን የተናገሩት ምክትል አሥተዳዳሪው በሰው ኃይል መቋቋም የሚቻለውን ለመቆጣጠር ጥረት ተደርጓል፣ ሰው በማይደርስባቸው ገደላማ አካባቢዎች ያለውን እሳት ግን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ነው ብለዋል። እሳቱ ከገደሉ እንዳይወጣ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።
ቃጠሎውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር እና ለማጥፋት ከፍተኛ የሕዝብ ንቅናቄ እንደሚጠይቅም አንስተዋል። ከዞኑ አቅም በላይ የሚሆንበት እድል ከተፈጠረ እገዛ እንፈልጋለን ነው ያሉት። የአካባቢው ማኅበረሰብ የዓለም ሀብት የኾነውን ታላቅ ስፍራ ከቃጠሎ ለመታደግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
የአስጎብኚ ማኅበር፣ የፓርኩ ሠራተኛ፣ የዞን እና የወረዳዎች የሥራ ኃላፊዎች፣ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎችም ቃጠሎውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በንቅናቄ መውጣት እንደሚገባም አሳስበዋል። ቃጠሎውን በአጭሩ ለማስቆም የክልል እና የፌዴራል ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!