
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አምራች ኢንዱስትሪዎች በዓይነት፣ በጥራት እና በመጠን ምርቶቻቸውን እያሳደጉ መኾኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
የኢትዮጵያ ታምርት 2016 የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በአዲስ አበባ ዛሬ ተካሄዷል።
በኢትዮጵያ ታምርት ሩጫ ውድድር በወንዶች አትሌት ገመቹ ዲዳ፤ በሴቶች አትሌት ጌጤ ዓለማየሁ አሸናፊ ኾነዋል። በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለወጡት የ250 ሺህ፣ የ150 ሺህ እና የ100 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ሚኒስትሩ እንደገለጹት አምራች ኢንዱስትሪዎች በጥራት እና በመጠን ምርቶቻቸውን እያሳደጉ ነው። ይህንን ለማስተዋወቅ እና ማኅበረሰቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን እንዲጠቀም የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተዘጋጅቷል።
የውድድሩ 80 በመቶ የሚኾኑት ተወዳዳሪዎች ከአምራች ኢንዱስትሪዎች የተገኙ ሠራተኞች ናቸው ያሉት አቶ መላኩ የአምራች ዘርፉን ምርት እና ምርታማነት ማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ ምርትን ማስተዋወቅ እና ጤናማ ሠራተኛ ሊኖር ይገባል ብለዋል።
በወንዶች ውድድር አንደኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው አትሌት ገመቹ ዲዳ ለኢፕድ እንደገለጸው ውድድሩ በፉክክር የተሞላና ለታዳጊ አትሌቶች እድል የሚሰጥ ነው። የአትሌቶች ቁጥር በጨመረ ቁጥር በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ለቀሪው ዓለም ለማስተዋወቅ ይረዳል ብሏል።
የውድድሩ የሴቶች አሸናፊ አትሌት ጌጤ ዓለማየሁ በበኩሏ ታዳጊ አትሌቶችን መሠረት ያደረጉ የሩጫ ውድድሮች ማስፉፉት ይገባል። የሀገር ውስጥ ውድድርን ከማበረታታት ባለፈ ጤናማና ንቁ ሠራተኞች በተቋማት እንዲኖሩ ያደርጋል ብላለች።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!