ብልጭ ድርግም የሚሉት እሴቶቻችን!

64

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሀገር እንደ ሀገር የሚቆመው በጠንካራ እሴት ነው፡፡ ይህ እሴት ደግሞ ትውልድ እንደ ጅረት አንዱ አልፎ ሌላው ሲተካ እየተቀባበሉ ሲጠብቁት እና ሲያከብሩት ሀገርን ልክ እንደ ማገር ኾኖ ያቆማል፡፡

እያንዳንዱ ዜጋ በሚያየው እና በሚረከበው የወላጆቹ፣ የጎረቤቶቹ ከፍ ሲም የሀገር እሴቶች መጠን ማንነቱ ይወሰናል፡፡ የሰው ልጅ ባየው እና በተማረው ልክ ይተገብራልና፡፡

ሀገራዊ እሴቶች በተግባር ሲውሉ ለአንድ ሀገር ጤነኛ የኾነ እንቅሰቃሴ እና ልማት ተግባር መዳረሻ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡

ከፍ ሲል በኢትዮጵያ ዝቅ ሲል ደግሞ እንደ ማኅበረሰብ ጠንካራ የሚባሉ ሀገራዊ እሴቶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ እሴቶች የሚቀዱት ደግሞ ከእምነቱ፣ ከባሕሉ እና ከማንነቱ ነው፡፡

እነዚህን እሴቶች ማክበር እና ማስከበር የሁሉም ዜጋ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከቤተሰብ እስከ ጎረቤት፤ ከአካባቢ እስከ ሀገር፤ ከሃይማኖት አባቶች እስከ ሀገር ሽማግሌዎች ሁሉም የየድርሻቸውን የሚወስዱት ጉዳይ ነው፡፡

አሁን አሁን ከዚህም ከዚያም የምንሰማቸውና ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ክስተቶች መነሻቸው አንደኛው ወደ ሌላኛው ጣቱን ከመቀሰር በዘለለ ሁሉም ለሚከሰተው የእሴት መበላሸት እና ጉዳት የድርሻውን ካለመውሰድ የመነጩ ናቸው፡፡

ብዙ ጊዜ ከቅርብ ከምላቸው ሰዎች በባሕላችን እና እሴታችን መሸርሸር እና አደገኛ አካሄድ ለመወያየት ስሞክር የማገኘው ምላሽም ይሄኑ ጣት መቀሳሰር እና አንዱ ሌላውን ኀላፊነቱን ባለመወጣቱ የመጣ ብልሽት እንደኾነ ከመግለጽ ባለፈ ለመፍትሔው ሲረባረብ እና ሲሠራ የምንመለከተው እንደሌለ ነው፡፡

በእሴቶች መሸርሸር እና መፍትሔዎቹ ዙሪያም ጉባኤ እና ምክክር ተሰናድቶ ብዙ ጊዜ ተመክሮበታል ግን ደግሞ ውጤቱ እዚህ ግባ የሚባል አልኾነም፡፡ ይህ ደግሞ ሄዶ ሄዶ ሀገራዊ ብልሽትን ማስከተሉ እና ሀገርን የሚያጠፋ ትውልድ መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡

እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ክልል ለእሴቶቻችን መሸርሸር የሚመለከታቸው ተቋማት መሥራት ያለባቸውን ሥራ አለመሥራታቸው እንዳለ ኾኖ ዘመኑ የወለደው ቴክኖሎጂ ይዞት ያመጣው የባሕል ወረራም ለችግሩ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡

አንዳንዶቹ መሠልጠንን የሚለኩት ከሀገራቸው እሴት ውጭ በሚያደርጉት የተሳሳተ ተግባር መኾኑ ችግሩ ምን ያክል ግዙፍ እንደኾነ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሄዶ ሄዶ ሀገራዊ የእሴት መገንቢያ የኾኑ ተቋማትን ማፍረሱ አይቀሬ ይኾናል፡፡

ይሁን እንጅ እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ማኅበረሰብ ያለው የእሴት መሽርሸር እንዳለ ኾኖ አልፎ አልፎ ብልጭ የሚሉት የሀገሪቱ መገንቢያ ማገር የኾኑት እሴቶች ጨርሶውኑ እንዳልጠፉ ማሳያም ናቸው፡፡

ከዚህ ጋር በተገናኘ በቅርብ የተፈጠረን ሁለት ጫፍ እና ጫፍ የኾኑ ተግባራትን እንመልክት። አንደኛው ተግባር በቅርቡ የሀገሪቱን ባንክ ህልውና የተገዳደረ ተግባርን ስናነሳ የሀገራችን እሴት የት እንደደረሰ የሚያሳይ ኾኖ እናገኘዋለን።

ይህም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሠራሩን ለማዘመን ሥራ በሚሠራበት ጊዜ የተፈጠረ ክፍተትን በመጠቀም የራስ ያልኾነን ገንዘብ ለመውሰድ የተደረገው ሩጫ እና እርስ በእርስ መረጃ እየተለዋወጡ ያውም በሌሊት በሚሊዮን የሚቆጠር የሀገርን ሃብት ለመዝረፍ የተደረገው ጥረት አሳዛኝ እና የራስ ያልኾነን ሃብት መንካት አይገባም እየተባለ ላደገ ሰው ጆሮን ጭው የሚያደርግ ክስተት ኾኖ አልፏል፡፡

ምንም እንኳን ባንኩ ሃብቱን ለማስመለስ በሠራው ሥራ አብዛኛው ገንዘብ ማስመለሱን ቢገልጽም ክስተቱ ግን አስገራሚ ነበር፡፡

በሌላ በኩል ከወደ ዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነዋሪ የኾኑት ወይዘሮ ስንዱ ደመቀ የተባሉ ግለሰብ ባጋጣሚ እጃቸው የገባን ገንዘብ የመለሱበት መንገድን ስንመለከት አበጁ ያስብላል፡፡

ጉዳዩን በቀላሉ ለማስረዳት ያክል ወይዘሮ ስንዱ ለሥራ ወደ ገበያ ለማቅናት ወደ አንድ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ ይገባሉ፡፡ አቶ እያሱ አስማማው የተባሉ ግለሰብም በተመሳሳይ ለሥራ ጉዳይ በባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ውስጥ ገብተው ጉዟቸውን ጀምረዋል፡፡ አቶ እያሱ ለመሬት ካሳ ክፍያ ያገኙትን 190 ሺህ ብር ይዘው ነበር ወደ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ ውስጥ የገቡት፡፡

በራሳቸው የግል ሃሳብ ላይ ሲብሰለሰሉ የቆዩት ግለሰቡ ከባለሦስት እግር ተሽከርካሪ ሲወርዱ ገንዘባቸውንም ጥለው ለመውረድ ተገደዱ፡፡ ገንዘቡን ከጥጋቸው የነበሩ ግለሰብ ትተው መውረዳቸውን የተገነዘቡት ወይዘሮ ስንዱ ደመቀ ገንዘቡን ለራሳቸው የችግር ጊዜ መውጫ ከማድረግ ይልቅ የራሳቸው ያልኾነ ገንዘብን በመጠየፍ ገንዘቡን ለፖሊስ ያስረክባሉ፡፡

ፖሊስም ገንዘቡን ተረክቦ በመዝገብ አሰፈረ፡፡ ገንዘቡን ጥለው የወረዱት አቶ እያሱ ለምናልባቱ በሚል ገንዘባቸውን ጥለው መውረዳቸውን ለፖሊስ አሳውቀው ኑሮ ፖሊስም ግለሰቦቹን በማገናኘት እንዲመሠጋገኑ አድርጎ ገንዘቡ ወደ ባለቤቱ እንዲመለስ አድርጓል፡፡

ይህን ክስተት በዓይነ ህሊናየ ስቃኘው እውነትም መልካም እሴቶቻችን ፈጽመው እንዳልጠፉ እና ተስፋ እንዳለን በማሰብ ኩራት ይሰማኛል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ባንክ እስከመዝረፍ የሚደርስ የትውልድ ክፋይ መኖራቸውን ሳስብ ውስጤ ይቆጫል፡፡

የኾነ ኾኖ ሁሉም መልካም ባሕል እና እሴቶቻችን ጨርሰው እንዳይጠፉ ጣት መጠቋቆማችንን ትተን ትውልድ ለማስተማር እና ለመገንባት ልንረባረብ ይገባል፡፡ ይህ ሳይኾን ቢቀር መልሶ የሚጎዳው እና የሚያፈራርሰው በሀገሪቱ ያሉ የእሴት መገንቢያ ተቋማትን እንደኾነ አስበን ልንሠራ ይገባል ትዝብታችን ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሌማት ትሩፋት ሥራዎቻችን ዋናው መልዕክት የምግብ ሉዓላዊነታችንን ማረጋገጥ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ
Next article“አምራች ኢንዱስትሪዎች በዓይነት፣ በጥራት እና በመጠን ምርቶቻቸውን እያሳደጉ ነው” አቶ መላኩ አለበል