“የሌማት ትሩፋት ሥራዎቻችን ዋናው መልዕክት የምግብ ሉዓላዊነታችንን ማረጋገጥ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ

38

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሌማት ትሩፋት ሥራዎቻችን ዋናው መልዕክት የምግብ ሉዓላዊነታችንን ማረጋገጥ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ተናገሩ።

ሀገራዊው የሌማት ትሩፋት ሥራዎች የአንድ ዓመት ተኩል አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ዛሬ በሀዋሳ መካሄድ ጀምሯል።

የግምገማ መድረኩን በይፋ ያስጀመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ የሌማት ትሩፋት ሥራዎች እንደ ሀገር ሲጀመሩ አራት ዋና ዋና ዓላማዎች እንዳሉት ገልጸዋል።

ዓላማዎቹም ምርትን ማሳደግና ገበያን ማረጋጋት፣ የውጪ ንግድ ውስጥ መሳተፍ፣ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን መተካት እና የሥራ ዕድልን መፍጠር ነው ብለዋል።

ይህ ሥራ የምግብ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ ወሳኝ ስለሆነ የመላው ሕዝባችን፣ የባለሙያዎች እና የአመራሩን ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ የሚፈልግ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በሲዳማ ክልል የታየው ምርጥ ውጤት ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች መስፋት እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ደረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ የሌማት ትሩፋት መንደሮች መፍጠር መቻሉን እና የሲዳማ ክልል በዚህ ረገድ አኩሪ ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል።

ይህ ልምድ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መስፋት እንዳለበት ተናግረው በኅብረተሰቡ ውስጥ የተፈጠረው መነሳሳት የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ውጤት ለማምጣቱ አመላካች ነው ብለዋል።

በመድረኩ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባዎች እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ መሆኑን ከሲዳማ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ባለውለታዎች!
Next articleብልጭ ድርግም የሚሉት እሴቶቻችን!