የኢትዮጵያ ባለውለታዎች!

83

የ”ቃኘው ሻለቃ ጦር” በኮሪያ

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ሠራዊት በየጊዜው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን ለማስከበር የሚጣልበትን አደራ በአግባቡ መወጣቱን የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየዘመኑ መመስከራቸውን እናስታውሳለን።

ጦር ሠራዊቱ ሰላምን ለማስከበር ሁሌም የሚዘምተው በኅብረቱ፣ በተመድ ጥሪ እና ጥላ ሥር መኾኑ ደግሞ አውነተኛ ሰላም አስከባሪ መኾኑን በተግባር አሳይቷል ይባልለታል፡፡

ለምሳሌ:- “ጠቅል” በሚል ስያሜ ወደ ኮንጎ የዘመተው የኢትዮጵያ ሠራዊት የሰላም አምባሳደርነቱን ላሳየበት ወታደራዊ ሥነ ምግባር የተሞላበት እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአህጉሩ የሰላም አምባሳደርነቱን በሚገባ አስመስክሯል፡፡

ዛሬ ልናስቃኛችሁ የፈለግነው “የቃኘው ሻለቃ ጦር” በኮሪያ ስላደረገው ዘመቻ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ክቡር ዘበኛ 2ኛ ቃኘው ሻለቃ ጦር የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፤ ይህ ጦር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር ወደ ደቡብ ኮሪያ የዘመተው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር መጋቢት 30/1952 ወይም ሚያዚያ 8/1943 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ነበር፡፡

ሠራዊቱ ወደ ኮሪያ ሲንቀሳቀስ በወቅቱ የሀገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ከነበሩት ከግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ እጅ ሰንደቅ ዓላማ እና የጦር ሠራዊቱን ዓርማ በአደራ ተቀብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራዊትም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 7ኛ ክፍለ ጦር 32ኛው እግረኛ ሬጅመንት አካል በመኾን ለግዳጅ ተሰማርቷል፡፡ ይህ የሻለቃ ጦር በተሠማራበት የውጊያ ቀጣና ሁሉ ድል እያስመዘገበ የተረከበውን ሰንደቅ ዓላማ እና የጦሩን ዓርማ በክብር ከፍ አድርጎ በማውለብለብ የሀገሩን ስም በማስጠራት ግዴታውን በብቃት፣ በታማኝነት እና በጀግንነት ተወጥቷል፡፡

ወደ ኮሪያ የዘመተው የኢትዮጵያ “የቃኘው ሻለቃ ጦር” ከያዘው መሬት አንድ ‘ኢንች’ እንኳ ለጠላት አሳልፎ አልሰጠም፡፡ አንድም ወታደር በምርኮ አልተወሰደበትም፡፡ በመኾኑም የዓለምን ሕዝብ “አጃኢብ!” ከማስባል ባለፈ ኢትዮጵያውያን የውጊያ ችሎታቸውን ያሳዩበት እና ኢትዮጵያውያን በተፈጥሮ ተዋጊ ናቸው የሚለውን ሐሳብ ያረጋገጡበት አጋጣሚ ተደርጎ ይወሰዳል።

ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም አሥጊ በነበረው በዚሁ የኮሪያ ጦርነት ውስጥ ተዋጊ እግረኛ ጦሯን አሠልፋ ያስመዘገበችው አኩሪ ድል ለዓለም አቀፍ ተልዕኮ ብቁ ኾና እንድትገኝ አድርጓታል፡፡ ለዓለም ሰላም መከበር ያላትንም እምነት አስመስክራለች፡፡

የኮሪያ ሪፐብሊክ መንግሥትም “ለኢትዮጵያ የምንከፍለው ብዙ ዕዳ አለብን፤ በችግራችን ጊዜ የደረሱልን የኢትዮጵያ ዘማቾች ለሁለቱ ሀገሮች ወዳጅነት መመሥረት ምትክ የማይገኝለት አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ስለኾነም ውለታችሁን መክፈል ይገባናል” ብለዋል፡፡

በአምስት ሻለቃዎች ወደ ውጊያ የገባው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ከኮሪያ ሪፐብሊክ እና ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት የክብርና የጀግንነት ሜዳይ ተሸልሟል።

የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ ደቡብ ኮሪያ የዘመተበትን ሚያዚያ 8/1943 ዓ.ም ታሳቢ በማድረግ በየዓመቱ ከሚያዝያ 6 ቀን ጀምሮ የኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ እየተከበረ ይገኛል፡፡

በመረጃ ምንጭነት:-ኢፕድ፣ ስዋሰው ዶት ኮም እና ኢትዮ ሪፈረንስ ድረ ገጾችን ተጠቅመናል፡፡

————-//————— //———–//————

“የይቻላል እና የጽናት ተምሳሌትነት” ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ

ከመም እስከ ጎዳና ላይ ውድድሮች ክብረ ወሰን የሰባበረው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ሚያዚያ 10 ቀን 1966 ዓ.ም በአሰላ ከተማ ተወለደ፡፡
ኃይሌ ሁለት የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ፣ አራት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና አራት የቤት ውስጥ ውድድሮችን አሸንፏል̀። 27 ክብረ ወሰኖችንም ሰብሯል።

ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ሩጫዎች የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ማኅበር በድረ ገፁ ይፋ እንዳደረገው ኃይሌ ገብረሥላሴ በሩጫ ዘመኑ በ410 ውድድሮች ያሸነፈ መኾኑን ገልጿል።

“የይቻላል እና የጽናት ተምሳሌትነት” ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ጎልህ አስተዋፅኦ ካላቸው ባለውለታዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ኃይሌ መቻልን በቃል ሳይኾን በድርጊት የሚኖር ብርቱ ሰውም ነው፡፡

“ከሌላ ዓለም የመጣ ፍጡር” እስከመባል የደረሰው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ብቃት እና ጀግንነት ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የናኘ ነው። ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ማሸነፍ ብቻ ሳይኾን አሸናፊነትን ክብረ ወሰንን በማሻሻል ያጀበው ብርቅዬው አትሌት 27 ክብረ ወሰኖችን በመሰባበር ጀግንነቱን አስመስክሯል።

ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ሀገሩን በዓለም መድረክ ከፍ አድርጓል። ለሀገሩ ክብር እና ኩራት አቅሙ የቻለውን ሁሉ ገብሯል። ላቡን እና እንባውንም አፍስሷል። ኢትዮጵያ የሰላም አየር ሲርቃትም ለሽምግልና ተሰልፏል።

አትሌቱ ለ28 ዓመታት በቆየበት ስፖርት ከ800 ሜትር አንስቶ በረጅም ርቀት የ10 ሺህ እና የ5 ሺህ ሜትር የመም እና የቤት ውስጥ ውድድሮችን አሸንፏል፡፡ ከአንድ ማይል እስከ 10 ማይል ርቀት፣ ከ10 እስከ 25 ኪሎ ሜትር በሚደርሱ የጎዳና ላይ ሩጫዎች እና በማራቶን ውድድሮች ድል ነስቷል፡፡ በአጠቃላይ እስከ 26 በሚደርሱ የሩጫ ዓይነቶች ላይ በመወዳደር እና አስደናቂ ውጤት በማስመዝገብ በታሪክ መዝገብ ስሙን በወርቅ ቀለም ያሰፈረ ሰው ነው።

ኃይሌን በቅርበት የሚያውቁት የውድድር ተካፋይ ኾኖ በዓለም አቀፍ መድረኮች ሲቀርብ፣ የሀገርን ክብር እንጂ ገንዘብን እንደማያስብ ይናገራሉ። እርሱም “ከእያንዳንዱ ድል በኋላ ገንዘብ ይከተላል” ይላል።

የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ፕሬዚዳንት የኾኑት እንግሊዛዊው ሎርድ ሴባስቲያን ኮው የዓለምን የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ ማነው ተብሎ ተጠይቀው ነበር። እሳቸውም “ለእኔ የምንግዜም ምርጥ ኃይሌ ገብረሥላሴ ነው፡፡ በረጅም ዓመታት የሩጫ ዘመኑ፣ በብዙ ርቀቶች በመወዳደር እና በተደጋጋሚ የዓለም ክብረ ወሰኖችን በማስመዝገብ የሚፎካከረው ስለሌለ” በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ከአየርላንድ እና ከሊድስ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ሽልማት አግኝቷል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኾኖ ያገለገለው ኃይሌ በሆቴል እና ቱሪዝም፣ በሪል ስቴት፣ በእርሻ፣ በማዕድን፣ በተሽከርካሪ መገጣጠም፣ በሚዲያዎች እና በፋይናንስ ተቋማት፣ በታላቁ ሩጫ፣ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ውስጥ በመሰማራት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያፈሰሰ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጐች የሥራ እድል በመፍጠር ሀገር ወዳድነቱን በተግባር ያስመሰከረ ብርቅዬ ኢትዮጵያዊ ነው።

በመረጃ ምንጭነት ኢቢሲ ኒውስ1፣ ኢትዮሪፈረንስ እና ቢቢሲ ናቸው፡፡

————-//————–//———-//———–

የአጼ ቴዎድሮስን ራዕይ ያስቀጠሉ ንጉሥ – ዋግ ሹም ጎበዜ

አጼ ተክለጊዮርጊስ (ዋግ ሹም ጎበዜ) በታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ያላቸው ነገር ግን ብዙም የማይነገርላቸው የሀገር ባለውለታ ናቸው፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ከሞቱ በኋላ ምኒልክ፣ ዋግሹም ጎበዜ እና በዝብዝ ካሣ በየአካባቢያቸው “እኔ ነኝ የምነግሥ” በሚል ሽኩቻ ውስጥ ገቡ፡፡

አጼ ቴዎድሮስ ለአንድነቷ የደከሙላት እና የሞቱላት ኢትዮጵያ በዚህ ጊዜ ተከፋፍላ የሦስት ነገሥታት ሀገርም መሰለች። ሦስቱም በተለያዩ ሦስት አውራጃዎች ቢገኙም በአንድ ባሕል፣ በአንድ ብሔራዊ የአማርኛ ቋንቋ፣ በአንድ ሃይማኖት የሚጠቀሙ ለአንዲት ኢትዮጵያ የሚያስቡ ኾነው ሳለ የተከፋፈሉት “እኔ ላስተዳድር” በሚል ነበር።

የኾነ ኾኖ የእንግሊዝ ጦር መቅደላን ለቅቆ ሲወጣ ዋግ ሹም ጎበዜ በነበራቸው የኃይል ሚዛን ማየል በዋግሹምነት ጠቅላላውን ሀገር እንዲያሥተዳድሩ ይንገሡ ተባለ፡፡ በዕጨጌ ገብረየሱስ እጅም ተቀብተው ሚያዚያ 9/1860 ዓ.ም ነገሡ። ስመ መንግሥታቸው ተክለ ጊዮርጊስ ተባለ። ለተከታታይ ሦስት ዓመታትም የኢትዮጵያ መሪ ኾነዋል።

ዋግ ሹም ጎበዜ አጼ ቴዎድሮስ ከሞቱ በኋላ ሀገሪቱን አንድ አድርጎ የመምራት ራዕይን ሰንቀው መትጋታቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ስለኾነም በታሪክ የአጼ ተክለጊዮርጊስ ሚና የኢትዮጵያን አንድነት አጠናክሮ ማስቀጠል በመኾኑ የአጼ ቴዎድሮስ ራዕይ ያስቀጠሉ ንጉስ ተብለውም ተወድሰዋል፡፡
ዋግ ሹም የሚለው ስያሜ በዋግ አካባቢ ለሹም የሚሰጥ የክብር ስም ነው።

አጼ ተክለጊዮርጊስ (ዋግ ሹም ጎበዜ) በዋግሹምነት ሀገር እንዲያስተዳድሩ የነገሱት በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 9/1860 ዓ.ም ነበር፡፡

ኢትዮሪፈረንስ እና ዎርልድፕረስ ዶት ኮም የመረጃ ምንጮቻችን ናቸው፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የሉዑክ ቡድን በሰሜን አሜሪካ የሥራ ጉብኝት እያደረገ ይገኛል።
Next article“የሌማት ትሩፋት ሥራዎቻችን ዋናው መልዕክት የምግብ ሉዓላዊነታችንን ማረጋገጥ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ