የኢትዮጵያ ታምርት የንቅናቄ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ መካሄድ ጀመረ።

35

ደሴ: ሚያዚያ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው “የኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” የንቅናቄ ፕሮግራም በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ተጀምሯል። በንቅናቄ መድረኩ የፌዴራል፣ የክልል አመራሮች እና የከተማዋ ባለሃብቶች ተገኝተዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የፋብሪካ እንዲሁም የኢንተርፕራይዝ ምርቶች ቀርበዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሀመድ አሚን የሱፍ በከተማዋ በ865 ሄክታር መሬት ላይ 58 ከፍተኛ እና መካከለኛ ፋብሪካዎች እያመረቱ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በከተማዋ ለሚገኙ 10 ሺህ 300 ዜጎችም የሥራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካዎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ30 ሺህ ቶን በላይ ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን አቶ መሀመድ አሚን ገልጸዋል።

በክልሉ የተፈጠረው ግጭት በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደፈጠረ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ ገልጸዋል። በዚህም ጥሬ እቃዎችን ለኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ እና ምርቶችን ለማከፋፈል እክል መፈጠሩን አንስተዋል፡፡

በችግር ውስጥም ኾኖ በክልሉ መዋለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ 57 አምራች ኢንዱስትሪዎች በዚህ ዓመት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ቢሮ ኀላፊው ጠቁመዋል።

በዘርፉ ላይ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ባልሃብቶች ወደ ማምረት እንዲገቡ እየተሠራ መኾኑንም አቶ እንድሪስ ገልጸዋል፡፡ በተለይም ለዜጎች የሥራ እድል እንዲፈጠር በማድረግ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ እንድታስቀጥል በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እና የክልሉን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት አምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግሥት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ በመኾኑ ሁሉም ለሰላም መጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣ አፈ ጉባኤ ፋንቱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡- ሰልሀዲን ሰይድ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በዲጂታል ጤና ፍኖተ ካርታ የመረጃ እና የህክምና ሥርዓቱን ለማዘመን እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ
Next articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ በሲዳማ ክልል የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ሥራዎችን ጎበኙ።