“በዲጂታል ጤና ፍኖተ ካርታ የመረጃ እና የህክምና ሥርዓቱን ለማዘመን እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ

39

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልላዊ የጤና እና ጤና ነክ መረጃ ቅመራ፣ ትንተና እና አሥተዳደር ማዕከል የትውውቅ መድረክ አካሂዷል፡፡ በመድረኩ ስለ ማዕከሉ አደረጃጀት እና አገልግሎት ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡

መድረኩን የከፈቱት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ በሀገር ደረጃ የሦስት ዓመት የጤና ዘርፍ ልማት ዕቅድ ውስጥ የመረጃ ሥርዓቱን ማዘመን እና መጠቀም አንዱ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ያለ መረጃ ውጤታማ መኾን እንደማይቻል የጠቀሱት ኀላፊው ለጤናው ዘርፍ መረጃ አሰባሰብ፣ ጥራት፣ አያያዝ እና አጠቃቀም ባለ ድርሻ አካላት ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡

በዚህም ችግሮች ተፈትተው ማኅበረሰባዊ ለውጦች ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በቀጣይም በዲጂታል ጤና ፍኖተ ካርታ የመረጃ እና የህክምና ሥርዓቱን ለማዘመን እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡

የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ የጤና እና ጤና ነክ መረጃ ለሀገር ያለውን ፋይዳ በመረዳት ለማጠናከር የምክክር መድረኩን አስፈላጊነት ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በክልሉ ጤና እና ጤና ነክ መረጃ ቅመራ፣ ትንተና እና አሥተዳደር ማዕከል በተለያዩ ተቋማት የሚገኙ መረጃዎች ከአጠቃላይ የጤና መረጃዎች ጋር ተሰባስበው ውጤት ባለው መንገድ ለሀገር በሚጠቅም ሁኔታ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ካንትሪ ዳይሬክተር እና የቀድሞው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ደሳለኝ መንገሻ (ዶ.ር) ከኅብረተሰብ ጤና ጋር የማይገናኝ መረጃ እንደሌለ ጠቅሰዋል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ነክ መረጃ ማዕከል ከአጋር አካላት ጋር ተባብሮ መሥራት ጠቀሜታው ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ እኛም እንደ አንድ አጋር አካል የመረጃ ማዕከሉ እንዲጠናከር ተባብረን እንሠራለን ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሔራዊ ጤና እና ጤና ነክ መረጃ ቅመራ፣ ትንተና እና አሥተዳደር ማዕከል ዳይሬክተር አስናቀ ወርቁ (ዶ.ር) የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጥንካሬ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ በሀገር ደረጃም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በተደረገ ጥናት ከ3 ሺህ 100 በላይ የጤና ዳታዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የጤናውን ዘርፍ ለማሳደግም የጤና መረጃዎችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ሴክተር መስሪያ ቤቶችም ያሏቸውን ጤና እና ጤና ነክ መረጃዎች በክልሉ የጤና መረጃ ቋት እንዲያስቀምጡም አሳስበዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ሙሉሰው አንዷለም (ዶ.ር) ጤና ኢንስቲትዩቱ የትውውቅ እና ግንዛቤ ፈጠራ ማመቻቸቱ ለቀጣይ ሥራዎች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ከአጋር አካላት ጋር ተባብሮ በመሥራት ለውጤት እንዲተጋ አሳስበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ አዲስ አምራች ኩባንያ ተመርቆ ሥራ ጀመረ፡፡
Next articleየኢትዮጵያ ታምርት የንቅናቄ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ መካሄድ ጀመረ።