በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ አዲስ አምራች ኩባንያ ተመርቆ ሥራ ጀመረ፡፡

33

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ባቲ ትሬዲንግ የተሰኘ ኩባንያ የማምረቻ ሼድ ውስጥ ማምረቻ ማሽነሪዎችን በመትከል እና በመገጣጠም በዛሬው እለት በይፋ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል።

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ፣ የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ መሀመድ አሚን የሱፍ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በጋራ ኩባንያውን ሥራ አስጀምረዋል።

በሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ ባቲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽኑ አቅም ላላቸው ሀገር በቀል ኩባንያዎች የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለውም አሁንም አቅም ያላቸው ሀገር በቀል ኩባንያዎች እና ባለሃብቶች ኮርፖሬሽኑ ተግባራዊ ያደረገውን ያጠረ የቢሮክራሲ አሠራር እና ዘርፈ ብዙ ማበረታቻዎችን በመጠቀም ወደ ኢንቨስትመንት እንዲመጡ ጋብዘዋል።

በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዛሬው እለት በይፋ ተመርቆ ሥራ የጀመረው ባቲ ትሬዲንግ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት በማድረግ ጥጥን በግብዓትነት በመጠቀም ክር የሚያመርት መኾኑም ተመላክቷል።

ከኮርፖሬሽኑ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ እንዳገኘነው መረጃ ኩባንያው አሁን ላይ 300 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡ ኩባንያው ምርቶቹን ሙሉ በሙሉ ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ የውጪ ምንዛሬን በማስቀረት በኩል ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ሐዋሳ ገቡ፡፡
Next article“በዲጂታል ጤና ፍኖተ ካርታ የመረጃ እና የህክምና ሥርዓቱን ለማዘመን እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ