ፍትሐዊ የመንገድ ተደራሽነት ጥያቄዎችን በዘላቂነት የሚፈታ የመንግድ ልማት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

32

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ስድስት ዓመታት በመላው ሀገሪቱ 5 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ተገንብቶ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገልጿል።

በኢትዮጵያ መንገድን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በጊዜ እና በጥራት ከማከናወን አኳያ ጉልህ ችግር እንደነበረባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ለሕዝብ ጥቅም የሚገነቡ መሰረተ ልማቶች እየተጓተቱ የመልካም አሥተዳደር ችግር ምንጭ ሲኾኑም ይስተዋላል።

የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ባለፉት ስድስት ዓመታት በመንገድ ልማት ዘርፍ የለውጡ መንግሥት የፍጥነት እና የጥራት ችግሮችን በመፍታት ለሕዝብ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ፍትሐዊ ምላሽ ለመስጠት ሰፊ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እስከ ለውጡ ዋዜማ ድረስ 12 ሺህ 900 ኪሎ ሜትር የመንገድ ሽፋን እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው ባለፉት ስድስት ዓመታት በተሠራው ሥራ 5 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ መንገድ ተገንብቶ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል።

ይህም ከተደራሽነት እንዲሁም ጉዞን ከማሳጠር አንጻር ይነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ ከ8 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር በላይ የሚኾኑ አዳዲስ የአስፋልት መንገዶች እየተገነቡ መኾናቸውን ጠቁመዋል። እነዚህ መንገዶች ወደ ሥራ ሲገቡ ከዚህ በፊት ይነሱ የነበሩ ፍትሐዊ የመንገድ ተደራሽነት ጥያቄዎችን በዘላቂነት እንደሚፈቱም ነው የገለጹት።

በግንባታ ላይ ካሉ መንገዶች ውስጥ አንዳንዶቹ ከዚህ ቀደም አስፋልት በጭራሽ ባልነበረባቸው አካባቢዎች የሚገነቡ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም 9 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት የጥናት እና የዲዛይን ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

የፕሮጀክቶቹ ስርጭት ከዚህ ቀደም በቂ የመንገድ ሽፋን እና በቂ የመንገድ ጥግግት ያልነበራቸውን አካባቢዎች ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚከናወን መኾኑን ገልጸዋል። ባለፉት ስድስት ዓመታት የተገነቡ፣ በመገንባት ላይ ያሉ እና በዝግጅት ሂደት ላይ የሚገኙ የመንገድ መሰረተ ልማት ሥራዎች ወደ 23 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚጠጉ መኾኑን ገልጸዋል። ኢዜአ እንደዘገበው አሁን ላይ በሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ሲታዩ ሌሎች ሀገራት ያላቸውን የመንገድ ሽፋን የሚያህሉ መኾናቸውን ጠቁመዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከላኳችሁ እና ከሚከፍሏችሁ ኃይሎች ይልቅ ኢትዮጵያ ትበልጣለች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን የሚደግፍ የመግባቢያ ሰነድ ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (JICA) ጋር ተፈረመ፡፡