
በ17ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ ባሕር ዳር ከነማ እና ፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡
ባሕር ዳር ከነማ ከመቀሌ 70 እንደርታ ጋር መቀሌ ላይ ተጫውቶ ያለምንም ግብ ተለያይቷል፡፡ የባሕር ዳር ከነማ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጨዋታውን አስመልክቶ በስልክ ለአብመድ በሰጡት አስተያዬት ከመቀሌ 70 እንደርታ ጋር ያደረጉት ጨዋታ ከባድ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ወሰኑ አሊ እና ፍቅረ ሚካኤል በጉዳት ምክንያት አልተጫወቱም፡፡
በአንጻሩ መቀሌ 70 እንደርታ በደጋፊው ፊት ጠንካራ የጨዋታ እንቅስቃሴ ማድረጉን አሰልጣኝ ፋሲል ተናግረዋል፡፡ ባለሜዳዎቹ ሙሉ ኃይላቸውን ተጠቅመው ማጥቃትን መሠረት ያደረገ ጨዋታ አድርገዋል፡፡ ባሕር ዳር ከነማ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት የጎል እድሎችን ፈጥሮ ወደ ግብ መቀየር አልቻለም፡፡ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እንደተናገሩት ቡድኑ ወደ መቀሌ ሲያመራ ለማሸነፍ ወይም ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት ነበር፡፡ በመሆኑም አቻ በመውጣታቸው እንዳላስከፋቸው በመግለጽ ተጫዋቾች በሜዳ ውስጥ ባደረጉት እንቅስቃሴ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ ከጠንካራ ቡድን ጋር ተጫውቶ ነጥብ መጋራት ተጫዋቾች ቀጣይ ከሜዳ ውጪ ለሚያደርጉት ውድድር ጥሩ የስነ-ልቦና መነቃቃት እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡ በተለይም የሊጉ መሪዎች ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ ባሕር ዳር ከነማ ለሻምፒዮንነት ለሚያደርገው ፉክክር ጠቃሚ እንደሚሆንም ነው የተናገሩት፡፡
ለቡድኑ መቀሌ ላይ በጣም ጥሩ መስተንግዶ እንደተደረገለትና ስታዲዮም ውስጥም ጥሩ የጨዋታ ድባብ እንደነበረ ነው አሰልጣኝ ፋሲል የተናገሩት፡፡
በ17ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ መርሃ ግብር ዛሬ ሰባት ጨዋታዎች ተደርገዋል፡፡ ፋሲል ከነማ ከሜዳው ውጭ ከድሬዳዋ ከነማ ጋር ያደረገው ጨዋታ ያለምንም ግብ ተጠናቅቋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከሰበታ ከተማ ጋር ተጫውቶ 1 ለ 0 ተሸንፏል፡፡ ጅማ አባጅፋር ከኢትዮጵያ ቡና ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ነው የተጠናቀቀው፡፡ ስሑል ሽረ ደግሞ ሲዳማ ቡናን 2ለ1 አሸንፏል፡፡ ወላይታ ላይ ወላይታ ድቻ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ተጫውተው ያለምንም ግብ አጠናቅቀዋል፡፡ የሐዋሳ ከተማ እና የሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ ደግሞ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ነው የተጠናቀቀው፡፡
ፋሲል ከነማ 30 ነጥቦችን በመያዝ በፕሪሚዬር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በመሪነት ተቀምጧል፡፡ መቀሌ 70 እንደርታ በ29 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሸነፉን ተከትሎ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል፡፡
በደጀኔ በቀለ