
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጫካ እና በአንዳንድ ስፍራ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ከላኳችሁ እና ከሚከፍሏችሁ ኃይሎች ይልቅ ኢትዮጵያ ትበልጣለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገለጹ። የለውጡን መንግሥት የሚደግፍ ሕዝባዊ መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።
በሕዝባዊ መድረኩ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በጫካ እና በአንዳንድ ስፍራ የሚትገኙ ኃይሎች ከከፋፋይነት፣ ከሰፈርተኝነት፣ ከመንደር እሳቤ ነጻ ወጥታችሁ ወደ ኢትዮያዊነት ከእኛ ጋር እንድታድጉ በጉራጌ ሕዝብ ስም ጥሪ አቀርባለው ብለዋል።
የእኛ የቋንቋ፣ የባሕል፣የአቀማመጥ ልዩነት ኢትዮጵያን የሚበትን መሆን የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ አንድነት እና አብሮነት ለመማር የጉራጌን ባሕል መገንዘብ ጠቃሚ ነው ብለዋል። ልዩ ልዩ ቋንቋ ብንናገር የተለያየ እምነት ቢኖረን እና ፆታችን ቢለያይ ኢትዮጵያ አንድ የምታደርገን በመሆኗ ለኢትዮጵያ አንድነት በጋራ የምንቆም እንሁን ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጉራጌ “ጎጎት”በተባለ ቃልኪዳኑ ስለ አንድነት ያስተማረ ፤ አንድነት ኃይል ነው ብሎ የሚያምን፤ በአንድት የሚገኘውን ፀጋ በልምድና በሕይወቱ የተገነዘበ መሆኑን ገልጸዋል። ጉራጌ ስለ ሰላም ያስተምራል ፤ በሰላም ይኖራል ፤ ሰላምን ያስተጋባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ሰላም ሳናስብ ሳንናገር ሰላምን ልንጎናፀፋት አንችልም ብለዋል።
የበለፀገች የማትለምንን ኢትዮጵያ ለማየት ሁላችንም በጋራ መቆም እንድንችል እና የሳታችሁ ወንድሞቻችን ልቦና እንዲሰጣችሁ እኔ እና የወልቄጤ ኅዝብ በጋራ መልዕክት እናስተላልፋለንም ብለዋል። ዘገባው የኢቢሲ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!