ከፈረስ ወደ ትራክተር እርሻ የተሸጋገሩት አርሶ አደር!

40
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት አየተሠራ ይገኛል። የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ዘመናዊ አስተራረስ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል።
በ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን የታቀደውን ምርት ለማሳካት ዘመናዊ የእርሻ ትራክተር አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ ተቀምጧል፤ ከ80 በላይ ተጨማሪ ኮምባይነር እና ትራክተሮች ተሰራጭተዋል። በዚህ ዓመት የኩታ ገጠም እርሻ ተግባራዊ ካደረጉ አርሶ አደሮች መካከል በደባርቅ ወረዳ ኪኖ መንደር 2 ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ሙሐባው አታክልት ይገኙበታል። አርሶ አደሮች የተሻሻሉ አሠራሮችን ተቀብለው በመተግበር ግንባር ቀደም ናቸው።
ከዚህ በፊት የግብርና ምርምር ምክረ ሃሳብን በመተግበር ምርጥ ዘር፣ ስንዴ እና የቢራ ገብስ በስፋት በማምረት ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ይታወቃሉ። ባገኙት ገቢም በደባርቅ ከተማ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ሁለት ቤቶችን መገንባት ችለዋል። በታታሪነታቸውም ክልል ድረስ እውቅና ማግኘታቸውን ነግረውናል።
በዚህ ዓመትም በቀበሌው የኩታ ገጠም የትራክተር እርሻን በመተግበር ከግንባር ቀደም አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ኾነዋል። ተሞክሮውን የወሰዱት ደግሞ በ2015/16 ዓ.ም የምርት ዘመን በአካባቢው የተደራጁ ወጣቶች በቀበሌ ጽሕፈት ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች መሬት ላይ በመተግበር ካገኙት ውጤት እንደኾነ ነግረውናል። አሠራሩ ጉልበት ቆጣቢ እና በምርት ደረጃም ውጤታማ ኾኖ በመገኘቱ የአካባቢው አርሶ አደሮች በመደራጀት በኩታገጠም እያሳረሱ እንደሚገኙ ገልጸውልናል። ከፈረስ ወደ ትራክተር መዞራቸውን በማንሳት፡፡
አርሶ አደር ሙሐባውም ሁለት ሄክታር ተኩል መሬት ማሳረሳቸውን ገልጸዋል። በዚህም እስከ ሦስት ጊዜ ለማረስ እስከ ሦስት ወራት ይወስድ የነበረው ማሳ በሰዓታት ውስጥ ማጠናቀቅ ችለዋል። በአካባቢው የሚታረሰው በፈረስ እንደመኾኑ ለአንድ ጥንድ ይሳተፍ የነበረውን የፈረስ ጎታች፣ የጎልጓይ እና የአራሽ ጉልበት እና የሚወስደውን ጊዜ አስቀርቷል። በተለይ በዘር ወቅት ተማሪዎችን ከትምህርት ቤት እስከማስቀረት ይደርሱ እንደነበረ ነው የነገሩን።
በአማራ ክልል ግብርናውን ለማዘመን በሜካናይዝድ ለማገዝ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰፊ ጥረት መደረጉን በምክትል ርዕስ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
በዚህ ዓመትም ተጨማሪ ከ80 በላይ ኮምባይነር እና ትራክተሮች በማሰራጨት የክልሉን ትራክተር ቁጥር ከ1 ሺህ 800 በላይ፣ የኮምባይነር ቁጥር ደግሞ ወደ 35 ማሳደግ መቻሉን ነው የገለጹት። የሚያጋጥሙ ቴክኒካል ችግሮችን ቀድሞ በመጠገን ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ያነሱት ኀላፊው ከቦታ ቦታ በማዟዟር አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግም ነው ያነሱት።
በክልሉ አርሶ አደሮች በማኅበር ተደራጅተው የትራክተር ግዥ እየፈጸሙ መኾናቸውን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ ክልሉ ካለው ሰፊ የሚታረስ መሬት እና ካለው ብዙ የሕዝብ ቁጥር አኳያ አሁንም ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየለውጡን መንግስት የሚደግፍ ሕዝባዊ መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
Next article“ከላኳችሁ እና ከሚከፍሏችሁ ኃይሎች ይልቅ ኢትዮጵያ ትበልጣለች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)