
ደብረ ማርቆስ: ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት አጥፊውን ኃይል ከሰላማዊው ሕዝብ ነጥሎ በወሰደው እርምጃ በአካባቢዉ ሰላም አየሰፈነ መምጣቱን የደጀን ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ሰውነት ገልጸዋል፡፡ አሥተዳዳሪው በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ የተሰማራው ኮር በጽንፈኛው ኃይል ላይ በተለያዩ ጊዜያት በወሰደው ጠንካራ እርምጃ አንጻራዊ ሰላም በመፈጠሩ ኅብረተሰቡ መደበኛ ሥራውን ያለ አንዳች ስጋት እያከናወነ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል፡፡
አስተዳዳሪው እንዳሉት በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጽንፈኞች ከኢትዮጵያ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመላላክ አንድነቷን ለማናጋት ዕኩይ ሴራ ነድፈው ሲሠሩ ነበር፡፡ ነገር ግን በመከላከያ ሠራዊት ብርቱ ክንድ ተመትተው ሕልማቸው ሳይሳካ ቀርቷል ብለዋል አቶ ጌታቸው፡፡ በወረዳው 21 ቀበሌዎች ላይ የተሰማራው ኮር ግዳጁን በብቃት በመወጣቱ ለወረዳው ሕዝብ እፎይታ የሰጠ ስኬታማ ተግባር መከናወኑንም ተናግረዋል፡፡
ዋና አሥተዳዳሪው “የጎጃም ኮማንድ ፖስት በእረፍት አልባ የግዳጅ ውሎ ከደም ጠብታ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ባጎናጸፈን ድል የወረዳችን ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል” ነው ያሉት፡፡ ሕዝቡ የተፈጠረውን ሰላም ተጠቅሞ በርካታ የልማት ሥራዎችን ማከናወኑንም ተናግረዋል፡፡
ሠራዊቱ የወረዳውን የፀጥታ መዋቅር በማጠናከሩ ሰላም ሰፍኗል፤ የማዳበሪያ ሥርጭት 50 በመቶ ተሳክቷል፤ መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት ተጠናክሮ ቀጥሏል፤ የጤና ተቋማት በሁሉም ቀበሌዎች አገልግሎት እየሠጡ ናቸው እንዲኹም 30 ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው፡፡
ሠራዊቱ ከመደበኛ ግዳጁ ጎን ለጎን በደጀን አካባቢ የትኖራ እና ጢቅ ቀበሌዎች ረጂ እና ደጋፊ ለሌላቸው ወገኖች ከኪሱ እና ከሚበላው ሬሽን ጭምር አካፍሎ ደግፏል። ልጆቻቸውን የማስተማር አቅም ለሌላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የትምህርት ቁሳቁስ ገዝቶ በመስጠት የሕዝብ አለኝታነቱን በተግባር ማረጋገጡንም ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል። ለዚህም በጎ ተግባሩ በወረዳው አሥተዳደር ስም ምስጋና አቅበዋል፡፡
መረጃው የጎጃም ኮማንድ ፖስት ነው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!