
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርዕሰ መምህራን፣ ሱፕርቫይዘሮች እና የትምህርት አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች እና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ያለመ የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ኮሚሽነር ደጀኔ ልመንህ እንደገለጹት የውስጥ ችግሮቻችንን ለመፍታት መደማመጥ እና መግባባት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የጸጥታ ችግሩ በአማራ ክልል የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ችግር መኾኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ የሰላምን ዋጋ መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል። ሰላምን ለማስፈን በመመካከር መሥራት እንደሚገባም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። በጎንደር ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቻላቸው ዳኘው “ሰበበኝነት ላይ በማመጽ የእኛን ዘመን አሻራ እናሳርፍ” በሚል ርእስ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል። ኀላፊው ሰበበኝነት በራስ ችግር ላይ ባለመንቃት ይጀመራል ብለዋል፡፡
አቶ ቻላቸው ዘላቂ ሰላም በአንድ አካል ብቻ የሚመጣ አይደለም ነው ያሉት። ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። ልማት የሁሉም ነገር ዋነኛ መውጫ መንገድ በመኾኑ ልማታዊ ትውልድ መገንባት እንደሚገባም አስረድተዋል። አካታች እና ፍታሐዊ አካሄድን በመዘርጋት ብልሹ አሠራርን በማረም የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል። አንዱ ችግር ሲፈታ ሌላውን ችግር ሊፈታ የሚያስችል ሥራ መሥራት እንደሚገባ አቶ ቻላቸው ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኃላ ከችግሮች በመላቀቅ ዘላቂ ሰላም እና ልማት መገንባት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ለዚህም በመገፋፋት ሳይኾን በጋራ ገመድ እና ውል መተሳሰር የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ግድ ይላል ብለዋል። ምክትል ከንቲባዋ ትምህርት ቤቶች እንዳይቆሙ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። አንድ በመኾን የተጋረጠውን አደጋ ለመቀልበስ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ማኅበረሰቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ነፃነት መንግሥቴ ውይይቱ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማስቀጠል ግብዓት የተገኘበት እንደኾነ ተናግረዋል። መምሪያው ከክፍለ ከተማ አመራሮች ጋር በጋራ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የትምህርት አመራሮች እና ባለሙያዎች ትምህርትን በጥብቅ ሥነ ምግባር እና ክትትል መምራት እንደሚገባቸውም ኀላፊዋ አሳስበዋል።
መረጃው የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!