የጸጥታ ችግሩ የታቀደውን ገቢ ለመሠብሠብ እንቅፋት እንደፈጠረበት የሰሜን ሸዋ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።

28

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ግብር መክፈል ለአንድ ሀገር እድገት እና ልማት ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ነው ያለው መምሪያው ግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ ግብሩን በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስቧል። የሰሜን ሸዋ ዞን ገቢዎች መምሪያ የጸጥታ ችግሩ የታቀደውን ገቢ ለመሠብሠብ ተግዳሮት እንደኾነበት ነው የገለጸው።

በመምሪያው የግብር ትምህርት እና ኮሙኒኬሽን ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ እሸቱ ሽፈራው በጸጥታ ችግሩ ምክንያት የታቀደውን ያክል ገቢ መሠብሠብ አልተቻለም ብለዋል። በበጀት ዓመቱ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ እስከ መጋቢት 2016 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ የዕቅዱን 40 በመቶ ያክል ብቻ መሠብሠቡን ነው የገለጸው።

ግብሩ በአብዛኛው የተሠበሠበው አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው ከተሞች መኾኑን የተናገሩት አስተባባሪው ወረዳዎች ላይ ተንቀሳቅሶ አለመሠራቱ ለገቢ አሠባሠቡ ችግር ኾኗል ብለዋል። የገቢ አሠባሠቡ ከ70 በመቶ በላይ መድረስ ነበረበት ያሉት አቶ እሸቱ የጸጥታ መታወኩ ደረሰኝ መስጠት ላይ ችግር ፈጥሯል ነው ያሉት። ይህ ደግሞ የገቢ አቅምን አዳክሟል ብለዋል።

በቀጣይ በዋና ዋና ከተሞች ደረሰኝ የመስጠት ክትትሉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት አቶ እሸቱ ግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል ከወለድ እና ከቅጣት መዳን እንደሚገባውም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ፋንታነሽ መሐመድ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር ምቹ አካባቢን በመፍጠር ለትውልድ ማስረከብ ይገባል” ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Next articleሰላማዊ መማር ማስተማርን ለማስፈን በመካከር መሥራት እንደሚገባ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ኮሚሽነር ደጀኔ ልመንህ ገለጹ፡፡