
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጤናማ እና ምቹ አካበቢን መፍጠርን ያለመ የአካባቢ ብክለት መከላከል ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ተካሂዷል። በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 91/1 ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጽዱ እና ጤናማ አካባቢ የመኖር መብት እንዳለው ይደነግጋል።
አካባቢን አለመንከባከብ ለሕይዎት መቀጠል መሠረታዊ የኾኑትን የአየር፣ የውኃ እና የአፈር ብክለትን ያስከትላል። ንቅናቄውን ያስጀመሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ “ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር ምቹ አካባቢን በመፍጠር ለትውልድ ማስረከብ ይገባል” ብለዋል፡፡ ጽዱ እና ጤናማ አካባቢን በመፍጠር ለትውልድ ማስረከብ እንደሚገባም በንግግራቸው አንስተዋል፡፡
የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን እና የተሽከርካሪ አጠቃቀማችንን በማዘመን አካባቢን ከብክለት የመከላከል ዘመቻውን በአግባቡ መተግበር ይገባል ነው ያሉት፡፡ በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዳይሬክተር ዲዳ ድሪባ አካባቢ ጥበቃን እና ብክለትን መከላከል ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል። በጽሑፉም በአየር፣ በውኃ፣ በአፈር እና በድምጽ ብክለት ምክንያት በጤና እና በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ እንደኾነ ገልጸዋል።
“ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ያለው የንቅናቄ መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የተዘጋጀ ሲኾን ለቀጣይ ስድስት ወራት ይካሄዳል ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!