
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በፍትሕ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በፌዴራል አሥተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅና በሽግግር ፍትሕ ፓሊሲ ዙሪያ ውይይት ተደርጓል። በውይይት መድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ.ር) የምክክር መድረኩን ዓላማ ካስተዋወቁ በኋላ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ በፖሊሲው እና ሥነ ሥርዓት አዋጁ የተዘጋጀውን የምክክር መድረክ በይፋ አስጀምረዋል። አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ መንገድ ለመተግበር የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። “አሥተዳደራዊ ፍትሕ የማኅበራዊ ፍትሕ የማዕዘን ድንጋይ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ባማከለ መንገድ የተዘጋጀ እና በመላ ሀገሪቱ ግብዓት ተሰብስቦበት የተዘጋጀ ፓሊሲ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!