
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ለክልላዊ እና ብሔራዊ ፈተናዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠራ መኾኑን የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታውቋል። በደሴ ከተማ አሥተዳደር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ሲሰጥ ቆይቷል። አሁንም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራው እንደቀጠለ ነው። በከተማዋ ለክልላዊ እና ብሔራዊ ፈተናዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ተብሏል።
ተወዳዳሪ እና ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት በትኩረት እየተሠራ መኾኑም ተመላክቷል። ተማሪዎችም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየተዘጋጁ መኾናቸውን ገልጸዋል። በደሴ ከተማ አሥተዳደር የሆጤ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ከፍል ተማሪው አቡበክር ዳውድ ለብሔራዊ ፈተናው ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን ተናግሯል። አስተማሪዎች ከመደበኛ ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ ተማሪዎችን ሊያዘጋጁ የሚችሉ ትምህርቶችን እየሰጧቸው መኾናቸውን ገልጿል።
ሙሉ ጊዜያቸውን ለዝግጅት እያዋሉ እንደኾነም ተማሪ አቡበከር ተናግሯል። ባለፉት ዓመታት የነበረው የፈተና አሰጣጥ እና የተመዘገበው ውጤት ተማሪዎች ላይ የሥነ ልቡና ጫና ቢኖረውም እንችላለን በሚል ስሜት የተሻለ ውጤት ለማምጣት እየተዘጋጀን ነው ብሏል። ለብሔራዊ ፈተናው ዋናው ጉዳይ ሥነ ልቡና ነው ያለው ተማሪ አቡበክር ፈተናዎችን አልፈን የተሻለ ውጤት እናመጣለን ነው ያለው። ተማሪዎች በመረጧቸው መምህራን አማካኝነት ለቅድመ ዝግጅት የሚረዱ ትምህርቶችን እየተማሩ መኾናቸውንም ተናግሯል። አስተማሪዎች ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ እያወጡ እንደሚሰጧቸውም ገልጿል። ከአሁን በፊት የነበሩ ፈተናዎችን እንደሚሠሩላቸውም ተናግሯል።
ሌላኛዋ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ዜና አላምረው በመምህራን እገዛ ዝግጅት እያደረግን ነው ብላለች። የአስተማሪዎች እና የወላጆች ድጋፍ የሚደነቅ መኾኑንም ገልጻለች። አስተማሪዎች ከተማሪዎች በላይ በቁጭት እንደሚደግፏቸውም ተናግራለች። ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት ውጤቶች ለተማሪዎች ከፍተኛ ጫና መፍጠራቸውን የተናገረችው ተማሪዋ “አናልፍም የሚለውን አመለካከት ሰብረን ለማለፍ እንሠራለን” ነው ያለችው።
በትምህርት ቤታቸው ቅዳሜ እና እሑድን ጨምሮ የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እንደሚያገኙም ገልጻለች። ጥረት ካለ የማይሳካ ውጤት እንደሌለም ተናግራለች። የሆጤ አጠቃላይ ሁለተኛ ድረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ጌታቸው መከተ ከኅዳር/2016 ዓ.ም ጀምረው ተማሪዎች በተመረጡ መምህራን ብሔራዊ ፈተና የሚሰጡ የትምህርት አይነቶችን የማጠናከሪያ ትምህርት እየሠጡ መኾናቸውን አስታውቀዋል። የተማሪዎችን ክፍተት በመለየት እየደገፉ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
መምህራን ከአሁን ቀደም በብሔራዊ ፈተና የወጡ ጥያቄዎችን እና ራሳቸው የሚያዘጋጇቸውን ጥያቄዎች እንደሚሠሩላቸውም ተናግረዋል። የሥነ ልቡና ጫናውን ለመቅረፍ በሥነ ልቡና ባለሙያዎች አማካኝነት እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። የመምህራን ተነሳሽነት እና ፍላጎት ከተማሪዎች በላይ መኾኑንም አመላክተዋል። ልጆቻቸው እንዲበቁላቸው እና ውጤታማ እንዲኾኑ የእረፍት ጊዜያቸውን ለማስተማር እንደሚጠቀሙበት ነው የተናገሩት። የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ፍቅር አበበ በከተማዋ ለክልላዊ እና ብሔራዊ ፈተናዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በከተማዋ ከሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በተሻለ መልኩ ሰላማዊ መማር ማስተማር መኖሩንም አስታውቀዋል። ተማሪዎችን ለክልላዊ እና ብሔራዊ ፈተናዎች ለማብቃት ዝግጅቱ ቀደም ብሎ መጀመሩንም አብራርተዋል።
ቅዳሜ በሁሉም ትምህርት ቤቶች በሚባል ደረጃ የትምህርት ቀን መኾኑን ገልጸዋል። ለተማሪዎች በተደጋጋሚ የሞዴል ፈተና እንዲወስዱ እየተደረገ ነው ብለዋል። አንደኛው የፈተና ችግር የሥነ ልቡና ነው ያሉት ኀላፊው የዩኒቨርሲቲ እና የኮሌጅ መምህራን ሥልጠና እንዲሰጡ መደረጉን ነው የተናገሩት። ተማሪዎች በሥነ ልቡና ዝግጁ ኾነው እንዲቀርቡ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የተማሪዎች የሥነ ልቡና ጫናዎችን ለመቅረፍ የሥነ ልቡና ሥልጠና እና ድጋፍ እስከመጨረሻው ድረስ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። በተቻለ መጠን ተማሪዎች መጻሕፍትን እንዲያገኙ ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል። አማራጮችን በሚገባ የተጠቀሙ ተማሪዎች ውጤታማ እንደሚኾኑም ተናግረዋል።
ለተማሪዎች ውጤታማነት የወላጆች ሚና ከፍተኛ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው ተማሪዎችን በመምከር እና በሥነ ልቡና በማዘጋጀት የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። መምህራን ውጤታማ ተማሪዎችን ለማፍራት እያደረጉት ያለውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል። ተማሪዎችም ሳይዘናጉ እና ሳይሰላቹ እስከመጨረሻው ቀን እንዲበረቱ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!