
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በኬንያ ጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡ የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የኬንያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጀኔራል ፍራንሲስ ኦሞንዲ ኦጎላን ህልፈተ-ሕይወት በማስመልከት የሀዘን መግለጫ አስተላልፈዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በሀዘን መግለጫቸው ጀኔራል ፍራንሲስ ኦሞንዲ ኦጎላ ለሀገራቸው እና ለቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት መረጋገጥ የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር አስታውቀዋል። እሳቸው እና ሌሎች ከፍተኛ መኮንኖችን ባጋጠማቸው የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ ሕይወታቸው በማለፉ በራሳቸው እና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ስም የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
ጀኔራል ፍራንሲስ ኦሞንዲ ኦጎላ ለኬንያ እና ለቀጣናው ሰላም እንዲሁም መረጋጋት ባበረከቱት አስተዋጽኦ ሁልጊዜ ሲታወሱ ይኖራሉ ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከኬንያ ወንድም ሕዝቦች ጋር መኾኑን አስረድተዋል። በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ መኮንኖች ቤተሰቦች እና ወዳጆች በራሳቸው እና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ስም መጽናናትን ተመኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!