በ2022 ኢትዮጵያን በአምራች ዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

22

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያን በ2022 ዓ.ም በአምራች ዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስርሩ መላኩ አለበል አስታውቀዋል፡፡ በተሻሻለው የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ እየተካሄደ ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በመክፈቻ ንግግራቸው እንደ ሀገር ያሉት ኢንዱስትሪዎች በተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ምክንያት ከአቅም በታች እያመረቱ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ ችግሮቹን ለመቅረፍ እና የአምራች ኢንዱስትሪውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ኹኖ መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡

የፖሊሲ ማሻሻያው ከኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጋር ተቀናጅቶ የሚካሄድ መኾኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ፖሊሲን ማሻሻል ብቻውን ግብ አይኾንም ያሉት ሚኒስትሩ አጋር አካላትም ተባባሪ ኹነው ለውጤታማነቱ እንዲሠሩ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባም አንስተዋል።

የተሻሻለው ፖሊሲ ከዚህ በፊት ከነበረው ፖሊሲ በተለየ ሁኔታ ገበያ መር፣ ለውጪ እና ተኪ ምርት ተመጣጣኝ ትኩረት የሚሰጥ፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን የሚያበረታታ፣ የምርት ልማት እና ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ እና የፋይናንስ አቅርቦት እና ተደራሽነት የተካተተበት ነው ተብሏል። ሁለት ዓመት የፈጀው የፖሊሲ ማሻሻያ ላይ የውጭ ሀገራት ባለሙያዎች መሳተፋቸውም ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዲያስፖራው ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደ ሀገር ቤት መላኩ ተገለጸ፡፡
Next articleግብርና ላይ ያተኮረ የብድር አሰጣጥ ሞዴልን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የፕሮጀክት ዕቅድ ላይ ምክክር ተደረገ።