ዲያስፖራው ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደ ሀገር ቤት መላኩ ተገለጸ፡፡

47

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ዓመታት የለውጥ ጉዞ በውጭ ግንኙነት እና በዲፕሎማሲው ዘርፍ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በተለይ በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሃብታዊ፣ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እና በሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ውጤቶች ተገኝተዋል ነው ያሉት፡፡

ቃል አቀባዩ ከፖለቲካ ዲፕሎማሲ አኳያ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲፈጠር የበኩሏን አስተዋጽኦ አድርጋለች በለዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላም ስምምነት ባሻገር በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በሱዳን እና በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ አዲስ የሰላም ንፋስ እንዲነፍስ ኢትዮጵያ የበኩሏን ጥረት አድርጋለች ነው ያሉት፡፡

እንደ አቶ ነብዩ ገለጻ በደቡብ ሱዳን እና በሶማሊያ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ጠንካራ ሰላም የማስከበር ሥራ ሲሠሩ ቆይቷል፡፡ ይኽም ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም፣ የኢኮኖሚ እና የሕዝብ ለሕዝብ ማኅበራዊ ትስስር እንዲጎለብት የሚረዱ ሥራዎችን በማከናወን ኢትዮጵያን የቀጣናው የስበት ማዕከል ኾና እንድትቀጥል እንዳስቻሏት ተናግረዋል፡፡ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነትም እያደገና እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል፡

ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ እንደ ትልቅ ድል የሚቆጠረው ኢትዮጵያ በቅርቡ የብሪክስ የጥምረት አባል መኾኗን አውስተው ጥምረቱ ለኢትዮጵያ አዲስ እና ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነትን የማስፋት እድል እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡ ከኢኮኖሚ ዲፕሎሎማሲ አኳያ ዋናው ስኬት በሀገር ውስጥ የሚሠራው ሥራ ነው ያሉት አቶ ነብዩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምግብ ራስን ለመቻል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠቃሽ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡ ራሱን በምግብ ያልቻለ ሀገር እና ሕዝብ የሌሎች ተላላኪ መኾኑ አይቀርምም ብለዋል፡፡

በበጋ ስንዴ ምርት በተሠራ ሰፊ ሥራ ውጤት መገኘቱም ነው የተገለጸው፡፡ በዚህም የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የአግሪኮላ ሽልማት እና እውቅና መስጠቱን አብራርተዋል፡፡ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በተመለከተ በተለያየ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ከማስመለስ ባለፈ የዜጎች መብት እና ክብር እንዲጠበቅ በኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በኩል ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡ ከዲያስፖራው ጋር ውይይቶችን በማድረግ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር ተሞክሯል ነው ያሉት፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በአማካኝ በዓመት 4 ቢሊዮን ዶላር ወደ ሀገር መላኩንም ገልጸዋል፡፡ በተሠራው ሥራም ዲያስፖራው ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደ ሀገር ቤት ልኳል፡፡ የበለጠ እንዲጨምር በመንግሥት በኩል ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ኢፕድ እንደዘገበው ዲያስፖራው ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከግድቡ ግንባታ መጀመር ጀምሮ በቦንድ ግዥ እና በስጦታ መልክ 55 ሚሊዮን ዶላር ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleነዋሪዎች አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ የወልድያ ከተማ አሥተዳደር አሳሰበ።
Next articleበ2022 ኢትዮጵያን በአምራች ዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡