ነዋሪዎች አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ የወልድያ ከተማ አሥተዳደር አሳሰበ።

28

ወልዲያ: ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ከሦስቱ ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በወቅታዊ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል። በወልድያ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋዬ ገብሬ የሕዝብን ጥያቄ ለማንፀባረቅም ይሁን መልስ ለማግኘት ኅብረት እና አንድነት ያስፈልጋል ብለዋል። የአካባቢን ደኅንነት ለመጠበቅም ኅብረት እና አንድነት ይሻል ነው ያሉት።

የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ሰርጎ ገቦችን በመቆጣጠር የከተማዋን ሰላም ለመጠበቅ ሕዝቡ ከአመራሮቹ ጎን ኾኖ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። መንግሥት ከሚያደርገው ሰላምን የማስከበር እርምጃ በተጨማሪ ነዋሪዎችም በየሰፈሩ በብሎክ በመደራጀት አካባቢያቸውን ሊጠብቅቁ ይገባል ነው ያሉት።

በየአደረጃጀቱ የግል ታጣቂዎችን ካልታጠቁ ነዋሪዎች ጋር በማቀናጀት የአካባቢውን የፀጥታ እና የደኅንነት ስጋት ለመቅረፍ ከተማ አሥተዳደሩ እንደሚሠራም ከንቲባው ገልጸዋል። በተለይም በየአካባቢው የሚያጋጥመውን ፀጉረ ልውጥ ለፀጥታ አካል በመጠቆም ነዋሪዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ነዋሪዎችም የአካባቢያቸውን ሰላም እና ደኅንነት በመጠበቅ ከመንግሥት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሠሩ ገልጸዋል። ከተማ ውስጥ የሚፈፀም የተኩስ ልውውጥ ለማንም አይጠቅምም፤ በየትኛውም ወገን የሚጎዱት ልጆቻችን ናቸውና ችግሩ በሰላም ይፈታ ሲሉም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡- ካሳሁን ኃይለሚካኤል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመድኃኒት መላመድ ዓለም አቀፋዊ አሳሳቢነት!
Next articleዲያስፖራው ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደ ሀገር ቤት መላኩ ተገለጸ፡፡