የመድኃኒት መላመድ ዓለም አቀፋዊ አሳሳቢነት!

57

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ላይ የኅብረተሰብ ጤና ችግር እየኾኑ ከመጡ የጤና ችግሮች ውስጥ የመድኃኒት ብግርነት አንዱ ነው። የመድኃኒት ብግርነት ማለት ለበሽታዎች የሚያገለግሉ መድኃኒቶች በሽታውን መላመድ ወይንም ምላሽ አለመስጠት ማለት ነው።

ባክቴሪያዎች ራሳቸውን ለማቆየት መድኃኒቶችን የሚቋቋሙበት ወይንም የሚላመዱበት ተፈጥሯዊ ሂደት አላቸው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ጅናቸውን በመቀየር በመድኃኒት እንዳይጠቁ ማድረግ አንዱ ስልት ነው። አሁን ላይ በዓለም ላይ የመድኃኒት ብግርነት (ምላሽ አለመስጠት) ዓለም አቀፋዊ ችግር እየኾነ መምጣቱን በአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የመድኃኒት ብግርነት አስተባባሪ ማይክል ጌቴ ገልጸዋል። ችግሩ በአፍሪካ እና ኤዥያ ሀገራት በስፋት ጎልቶ እንደሚታይ ነው አሥተባባሪው የገለጹት።

የዓለም ጤና ድርጅት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2019 የመድኃኒት ብግርነትን ዓለማቀፋዊ አሳሳቢነት አስመልክቶ ሪፖርት አውጥቶ ነበር። በዚህም በዓመት 1 ነጥብ 27 ሚሊዮን የሚኾን ሰው በቀጥታ በመድኃኒት ብግርነት ባክቴሪያ አምጭ ተህዋሲያን ምክንያት ይሞታል። ወደ 4 ነጥብ 95 ሚሊዮን የሚኾን ሰው ደግሞ በተዘዋዋሪ መልኩ በመድኃኒት ብግርነት ምክንያት ሕይወቱ ያልፋል። ድርጅቱ አፍሪካ ላይ ባደረገው ጥናት ደግሞ በዓመት 1 ነጥብ 05 ሚሊዮን ሰዎች በዚሁ ሰበብ ሕይወታቸው ያልፋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት የመድኃኒት ብግርነት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተጽዕኖው ከፍተኛ ነው። በሽታው መድኃኒቱን እየተላመደ ሲመጣ ሰዎች ያደጉ ምርመራዎችን ለማድረግ ለተጨማሪ ወጭ ይጋለጣሉ። ከዚህም ባለፈ ሰዎችን ለተለያዩ ማኅበራዊ ቀውሶች ያጋልጣል።

የዓለም ጤና ድርጅት የመድኃኒት ብግርነትን ለመከላከል ዓለም አቀፋዊ እቅድ አውጥቷል። በኢትዮጵያም ከ2021 እስከ 2025 ላብራቶሪን መሠረት ያደረገ ስትራቴጅክ እቅድ ወጥቶ ሲተገበር መቆየቱን ገልጸዋል። አሁን ላይም እሰከ 2030 (እ.አ.አ) የሚተገበር አንድ ጤናን ማዕከል ያደረገ ስትራቴጅክ እቅድ ተዘጋጅቶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ በአማራ ክልል እንደ ፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ደሴ ቅርጫፍ ላብራቶሪዎች የማይክሮ ባዮሎጂ ካልቸር ምርመራ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ በሆስፒታሎች የምርመራ መሣሪያዎች እጥረት እና የምርመራ ተደራሽነት ችግር እንዳለ ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት በአብዛኛው ሕክምናው በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ወይንም በ”ይመስላል፣ በሊኾን ይችላል” ለመስጠት አስገድዷል ብለዋል።

አሥተባባሪው እንዳሉት በቀጣይ የመድኃኒት ብግርነትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የማኅበረሰብ ግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ላይ ትኩረት ይደረጋል፤ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የአንድ ጤናን ሁሉን አቀፍ ትብብር ማሳደግ እና መሰል ሥራዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል። በቤተ ሙከራ ማዕከል ያደረገ የመድኃኒት ብግርነት ቅኝት፣ አሰሳ እና የምርመራ ሥራዎችን የማጠናከር ሥራ እንደሚሠራም ነው የገለጹት። ለዚህም የካልቸር ምርመራን የማጠናከር ሥራ ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል። በምርመራ ለተገኙ በሽታዎች የሚታዘዙ መድኃኒቶች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲወሰዱ ይደረጋል። ደረጃውን ሳይጠብቅ መድኃኒቶችን መውሰድ ለመድኃኒት ብግርነት ስለሚያጋልጥ አንድ ታካሚ ደረጃውን ሳይጠብቅ መድኃኒት መውሰድ እንደሌለበት መክረዋል። ማኅበረሰቡ የአካባቢ ንጽሕናን እንዲጠብቅ እና የመጠጥ ውኃን አክሞ እንዲጠቀም አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ
Next articleነዋሪዎች አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ የወልድያ ከተማ አሥተዳደር አሳሰበ።