ፊንላንድ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱን ለመደገፍ ቁርጠኛ መኾኗን ገለጸች፡፡

33

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምሥጋኑ አርጋ የአፍሪካ ቀንድ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ ከጀመሩት የፊንላንድ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ጉዳይ ልዩ መልዕክተኛ ሱልዳን ሰይድ አሕመድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምሥጋኑ አርጋ ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ የትብብር ግንኙነት አድንቀዋል፡፡ አምባሳደር ምሥጋኑ ፊንላንድ በቀጣይም በውኃ ዘርፍ፣ በግብርና እና በትምህርት ዘርፍ ያላትን ግንኙነት አጠናክራ እንድትቀጥል ልዩ መልዕክተኛውን ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ስታደርግ የነበረውን ጉልህ አስተዋጽኦ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አምባሳደር ምስጋኑ ገልጸዋል። የፊንላንድ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ጉዳይ ልዩ መልዕክተኛ ሱልዳን ሰይድ አሕመድ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ዋነኛዋ የፊንላንድ አጋር መኾኗን ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ትሠራለች ያሉት የሰላም ጉዳይ ልዩ መልዕክተኛው ሀገራቸው በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሀገራዊ ምክክር ለመደገፍ ቁርጠኛ መኾኗን ገልጸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ሀገራቱ በወቅታዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ተጠቃሚነትን የበለጠ በሚያጠናክሩ አግባቦች ላይ መክረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየብረት ምርትን ማሳደግ የሀገሪቷ የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ አካል መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናገሩ።
Next articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ