ትምህርት አቋርጠው የቆዩ ትምህርት ቤቶች ወደ ማስተማር ሥራ መመለሳቸውን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ፡፡

27

ደብረ ማርቆስ: ሚያዝያ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ትምህርት አቋርጠው የቆዩ 38 የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወደ ማስተማር ሥራ መመለሳቸውንም አስታውቋል፡፡ በደጀን ከተማ አሥተዳደር አሚኮ ያነጋገራቸው ተማሪዎች እና መመህራን በግጭት ምክንያት ተቋርጦ የቆየው ትምህርት በመጀመሩ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡

የዓድዋ ደም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በክልሉ በተከሰተው ግጭት ምክንያት ከቤቱ ርቀው የነበሩ ልጆቹን አግኝቷል። የተነፋፈቁ ጓደኛሞች ተገናኝተዋል። ዛሬ ላይ ግቢው በታዳጊዎች ደምቋል። ታዳጊዎችም የነገ ምኞታቸውን ወደሚነድፉበት የትምህርት ገበታ በመመለሳቸው ደስታ ከፊታቸው ይነበባል።

ተማሪ ይሄሩ ሸጋው እና ዓለም ለውጤ በደጀን ከተማ አሥተዳደር የዓድዋ ደም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው። ታዳጊዎቹ ነገን ወደ ሚያልሙበት ትምህርት ቤት በመመለሳቸው ደስተኛ ኾነዋል። በዚህ ዓመት ለሚሰጠው ክልል አቀፍ ፈተና እየተዘጋጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

መምህር ወንድወሰን ሙላት በክልሉ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለወራት ከተለያቸው ታዳጊዎች ጋር ዳግም ተገናኝተዋል፡፡ ተማሪዎችን በትጋት እያስተማሩ መኾናቸውንም ነግረውናል። የዓድዋ ደም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህርት ሰላም ጤናው በመምህራን እና በወላጆች ድጋፍ ወደ ትምህርት ገበታቸው የተመለሱ ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን እተከታተሉ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የደጀን ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተገኔ ኪዳነ ማርያም እንደገለጹት በአካባቢው የታየውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ በከተማ ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ቀደም ብለው ማስተማር ሲጀምሩ ባለፉት ሁለት ወራት ደግሞ በዙሪያው የሚገኙ 12 ትምህርት ቤቶች ማስተማር መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ተገኔ በግጭት ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን ትምህርት ለማካካስ መምህራን በቁጭት እየሠሩ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጌታሁን ፈንቴ ለወራት በዘለቀው ግጭት ምክንያት በዞኑ የትምህርት ልማት ሥራ ከገጠመው ማነቆ እና ስብራት ለማላቀቅ በተደረገው ብርቱ ጥረት ተስፋ ሰጭ ውጤቶች እየታዩ ነው ብለዋል። በግጭቱ ምክንያት ለወራት ትምህርት ያቋረጡ ትምህርት ቤቶችም ወደ መማር ማስተማር ሥራቸው እየተመለሱ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ጌታሁን በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባለፉት ሁለት ወራት አንጻራዊ ሰላም በታየባቸው አካባቢዎች 38 የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ተቋርጦ የቆየው የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዘላለም አስፋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleያለፉት ስድሰት ዓመታት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን አስጠብቃ መጓዝ የቻለችባቸው ዲኘሎማሲያዊ ድሎች የተገኙባቸው መኾናቸው ተገለጸ፡፡
Next article“ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም እንደ ሀገር ለጀመርነው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት ግንባታ ፋይዳው የጎላ ነው” አቶ ተመሥገን ጥሩነህ