
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ባለፉት ስድስት ዓመታት በውጭ ግንኙነት እና በዲፕሎማሲ ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች፣ በሳምንቱ የተከናወኑ ዋና ዋና የዲፕሎማሲ ሥራዎች እና በቀጣይ በታቀዱ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ላይ ያተኮረ መግለጫ ሰጥተዋል።
ያለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት የዲኘሎማሲ ሥራዎች በፈተና የታጀቡ አንፀባራቂ ድሎች የተገኙበት መኾኑን ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል። በኢኮኖሚ መስክ ማሻሻያዎችን በማድረግ ለውጭ ኩባንያዎች ዝግ የነበሩ መስኮችን በመክፈት፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ እና በዋናነት ደግሞ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የተሠሩ ሥራዎችን በአብነት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትኾን የተሠራው የዲፕሎማሲ ሥራ ትልቅ ስኬት የታየበት መኾኑን ገልጸዋል። ለአየር ንብረት የማይበገር ኢኮኖሚን ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ሀገር አቀፍ ጥረት በአረንጓዴ አሻራ እና በዲኘሎማሲ ሥራዎች ታግዞ ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኝ ብዙ መሠራቱንም ተናግረዋል።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ጉርብትናን ለማጠናከር እና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጎልበት የተሠሩ ሥራዎችንም ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል። እነኚህ የዲኘሎማሲ ሥራዎች በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና እድገትን ለማዝለቅ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል። የውጭ ተፅዕኖ እና ጣልቃ ገብነትን አጥብቆ በመከላከል መንግሥት እና ሕዝብ በታላቁ ህዳሴ ግድብ እና በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ግጭት የሀገርን ጥቅም አስጠብቆ ማዝለቅ ያስቻሉ ስኬቶችን ማስገባታቸው በመግለጫው ተነስቷል።
አቶ ነብዩ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካዊ ማዕቀፍ እንዲፈታ ባላት ያላሰለሰ ጥረት እና ፍላጎት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በመፈረም እና ገቢራዊ እንዲኾን በማስቻል ሀገሪቱ ለሰላም ያላትን ፅኑ ፍላጎት አስመስክራለች ብለዋል። ኢትዮጵያ መስራች በኾነችባቸው የባለብዙ ወገን ተቋማት ውስጥ ተሳትፎዋን በማጠናከር በተለይ በፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ድምጽ እያሰሙ ካሉ መሪ ሀገራት መካከል አንዷ እንደኾነች ተናግረዋል።
ነባር ግንኙነቶችን በማስቀጠል አዳዲስ የትብብር ምዕራፎችን በመክፈት በዲያስፖራ እና ዜጋ ተኮር ዲኘሎማሲ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ያስቻሉ ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ቃል አቀባዩ አመልክተዋል። በዲኘሎማሲ ተተኪ ትውልድ ለማፍራት እና መነቃቃትን ለመፍጠር በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የትሪሊየም ዓለምአቀፍ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንዲታደሙ ተደርጓል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!