
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በላይ አርማጭሆ ወረዳ የኅብረተሰብ ጥያቄ የነበረው የቁስቋም ሮቢት የጠጠር መንገድ ጥገና ተደርጎለት አገልግሎት በመስጠቱ መደሰታቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። የሮቢት ከተማ ነዋሪ አቶ አሻገረ መዝገቡ ቀደም ሲል የመንገድ ችግር እንደነበረ አንስተዋል። አሁን ላይ በክልሉ መንገድ ቢሮ መንገዱ ተጠግኖ የተሻለ አገልግሎት እያገኙ መኾናቸውን አስረድተዋል። አቶ አሻገረ እንደሚሉት ከዚህ በፊት መንገዱ አመቺ ባለመኾኑ ነብሰ ጡር እናቶች ወደ ጤና ተቋም ሄደው ለመውለድ ይቸገሩ ነበር፡፡
ሌላኛው የሮቢት ከተማ ነዋሪ መምህር ዳንኤል ከዚህ በፊት መንገዱ የከፋ ችግር እንደነበረበት አስረድተዋል። ኾኖም አሁን ላይ ጥገና ከተደረገለት ጊዜ ጀምሮ በተሽከርካሪዎች ላይ የታሪፍ መሻሻል መታየቱን ተናግረዋል። አቶ ምህረት ቸኮል በበኩላቸው የአካባቢው ኅብረተሰብ ከሰላም ሥራዎች ጎን ለጎን በልማት ሥራዎች ተሳታፊ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የላይ አርማጭሆ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አስረሳው ደሴ የቁስቋም ሮቢት የጠጠር መንገድ ፕሮጀክት 23 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ገልጸዋል። ሮቢት እና አካባቢው ካለው ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሃብት አንፃር መንገድ ባለመኖሩ ምክንያት ለከፍተኛ ኪሳራ ሲዳረጉ መቆየታቸውን ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል።
ይሁን እንጅ አሁን ላይ የመንገድ ፕሮጀክቱ ጥገና ተደርጎለት 16 ቀበሌዎችን እንደሚያገናኝ የገለጹት ዋና አሥተዳዳሪው ከ66 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፎሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አብራርተዋል። ጥገና የተደረገለት መንገዱ የግብዓት አቅርቦት ሥራዎችን እና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን ለማከናወን ጥሩ እድል እንደፈጠረላቸው ነው ያብራሩት፡፡ የአካባቢው ሕዝብ ባቀረበው ጥያቄ የክልሉ መንግሥት ለሰጠው ምላሽ አመሥግነዋል፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ አስንቃ ክብካብ በዞኑ በ14 መስመሮች 455 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ሥራ በክልሉ መንገድ ቢሮ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የመንገድ ግንባታ ሥራው ተጠናቅቆ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ከሚሠሩ መንገዶች ውስጥ የቁስቋም ሮቢት የጠጠር መንገድ ግንባታ ሥራው ተጠናቅቆ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። መንገዱ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈታ እንደኾነም አስረድተዋል።
የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የመንገድ አውታር ኮንትራት አሥተዳደር መሀንዲስ ባለሙያ አበራ ንፁህ በክልሉ ከ4ሺህ 560 ኪሎ ሜትር ያላነሱ የጠጠር መንገድ ፕሮጀክቶች በ812 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በግንባታ ላይ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የቁስቋም ሮቢት የጠጠር መንገድ ጥገና ፕሮጀክት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ እንዳለው በቀጣይ ተገቢውን የክትትል ሥራ አጠናክሮ በማስቀጠል እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እንደሚሠራም አስረድተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!