
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል፣ ለኢንዱስትሪ ምርት ግብዓት ለማግኘት እና ለገበያ የሚኾኑትን በማምረት የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት ከመኸር ሰብል ልማት በተጨማሪ በበጋ መስኖ ሰብልን ማልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።
አቶ ዘላለም እንዳላማው በፎገራ ወረዳ አርሶ አደር ናቸው፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታትም ስንዴን በበጋ መስኖ አምርተዋል፡፡ በበጋ አትክልትን እንጂ ሰብልን አናመርትም ነበር ያሉት አርሶ አደር ዘላለም አሁን ግን ስንዴን በማምረታችን ተጨማሪ ጥቅም እያገኘን ነው ብለዋል፡፡
የውኃ እጥረት እና የነዳጅ እንደልብ አለመገኘትን በችግርነት ጠቅሰዋል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልት እና ፍራፍሬ ከፍተኛ ባለሙያ አወቀ ዘላለም በበጋ መስኖ የሚለሙ ሰብሎች በክረምት ከሚለሙት ያነሰ የአደጋ ተጋላጭነት እና የተሻለ ምርታማነት አላቸው ብለዋል። ለዘርፉ ትኩረት በመስጠትም ከመኸር በተጨማሪ በበጋ መስኖ የማምረት ሥራ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል 333 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ መልማት እንደሚችል እና እስካሁን 285 ሺህ ሄክታሩ መልማቱን ባለሙያው ጠቅሰዋል። ቴክኖሎጂ፣ የተሻሻለ አሠራርን እና የባለሙያ ምክርን በመጠቀም እየተተገበረ ያለው የበጋ መስኖ ልማት ውጤታማነት በሄክታር እስከ 38 ኩንታል ምርት መድረሱን ገልጸዋል።
የአርሶ አደሮች የሞተር ነዳጅ ፍላጎት መጨመሩ፣ በውኃ አጠቃቀም ላይ ግጭት መጨመሩ እና በቆሎ ከጓሮ አልፎ በማሳ መመረቱ የበጋ መስኖ ተቀባይነት ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል። ኾኖም ግን ቴክኖሎጂ እና የተሻሻሉ አሠራሮችን መጠቀም ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት የተሠራው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ጎላ ብሎ ቢታይም አሁንም የበለጠ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በፕሮጀክቶች የማዳበሪያ፣ የዘር እና መሰል ድጎማዎች በማድረግ አርሶ አደሮችን ለማስተማር ግፊት ማድረጉ ቋሚ ስላልኾነ በዘላቂነት አርሶ አደሮች በራሳቸው በባለቤትነት እንዲሠሩ ይደረጋል ብለዋል።
አትክልትን በመስኖ ማምረት ለምርቱ የዋጋ ጭማሪ ሊያስገኝ ቢችልም ሁሉም አትክልት ባመረተ ጊዜ ደግሞ ዋጋው የመቀነስ ወይም ተበላሽቶ የማክሰር አደጋ እንደሚያስከትል ገልጸዋል። በበጋ መስኖ ሰብልን ማምረት ግን እንደ አትክልት ቶሎ ስለማይበላሽ እና ዋጋው ቢረክስ ማቆየት ስለሚቻል የማያከስር መኾኑ ተመራጭ እንደሚያደርገው ባለሙያው ጠቅሰዋል። ለሁሉም መፍትሔው ሰብል እና አትክልት በምን ያህል መጠን መመረት እንዳለበት አቅዶ ማምረት መኾኑን አቶ አወቀ ገልጸዋል።
በመስኖ ዘርፍ ግብርናውን ለማሳደግ ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ የገለጹት አቶ አወቀ አርሶ አደሮች የበለጠ እንዲያመርቱ ግን የግብርና ግፊት እና ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል። ”ድጋፋችንን የምናቆመው አርሶ አደሮች ራሳቸውን ችለው ሲያመርቱ እና በሄክታር ከፍተኛ የምርታማነት አቅም ላይ ሲደርሱ ነው” ብለዋል።
በበጋ መስኖ ልማት ምርታማነትን የሚቀንሱ ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ነው አቶ አወቀ የጠቆሙት፡፡ የስንዴ ሰብል በከፍተኛ ሞቃታማ ጊዜ ካበበ መሐን ኾኖ ምርቱ ሊቀንስ ስለሚችል ሙያዊ አሠራሮችንም አስቦ መሥራት ማስፈለጉን በምሳሌነት አንስተዋል። በበጋ መስኖ ስንት ኩንታል ምርት ተገኘ እንጂ ስንት ሄክታር ማሳ ተሸፈነ የሚለው መለኪያ መኾን እንደሌለበት ነው አቶ አወቀ ያሳሰቡት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!