ለኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስፈላጊውን የቅንጅት ሥራ በጋራ በመሥራት እንደሚያግዙ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

20

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን የአራት ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት አዳምጠዋል፡፡ በዚህ ወቅት “ለኮሚሽኑ የምናደርጋቸው ድጋፎች በሀገር ግንባታ ሥራችን ላይ አሻራ የምንጥልበት በመኾኑ አስፈላጊውን የቅንጅት ሥራ በጋራ በመሥራት ማገዝ ያለብንን የምናግዝ ይኾናል” ብለዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ ኀላፊነትን በተላበሰ መልኩ የተጣለበትን ተልዕኮ ለማሳካት የሚያገጥሙ ችግሮችን ተቋቁሞ የሕዝባችንን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ የሠራቸውን ሥራዎችን በጥንካሬ አንስተዋል። በሀገር ደረጃ ያሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ከችግሩ መቅደም ያስፈልጋል ብለዋል አፈ ጉባኤው፡፡ ለሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ተገዢ ኾነው እንዲሠሩ ከመንግሥት መዋቅር እና ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመመካከር አስፈላጊ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡

ሌሎች ድጋፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ተቋማት ጋር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በጋራ በመሥራት ለሀገሪቱ ሕዝብ የገባነውን ቃል መፈጸም ይኖርብናል ነው ያሉት አፈጉባኤው። የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች በርካታ የቅድመ ዝግጅት እና የተሳታፊ ልየታ ሥራዎች ማከናዎናቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልል ደረጃ የሚደረጉ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የምክክር ሂደቶችን አስመልክቶ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት በርካታ ሥራዎችን ማከናወናቸውንም ነው ያነሱት። በቀጣይም ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች ልየታ ባልተከናወነባቸው ክልሎች ልየታ በማድረግ አጀንዳዎችን በሕዝባዊ ውይይቶች በማሰባሰብ ምክክሮች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ሂደት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያግዙ የባሕል መሪዎችን የመለየት እና ተቀራርቦ የመወያየት ሥራዎችን እንሠራለን ነው ያሉት።

ኮሚሽነሩ በግጭት ምክንያት በክልሎች የተሳታፊዎችን ልየታ ሥራ ለማጠናቀቅ ችግር እንደኾነባቸው ሳይገልጹ አላለፉም ። በምክክር ሂደቱ ውጤታማ እና በሀገሪቱ የተሻለ የሰላም እና የፖለቲካ መደላድል እንዲፈጠር ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረከት እንደሚገባም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች ጨምሮ የመንግሥት ተጠሪዎች፣ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና አባላት እንዲሁም የምክር ቤቱ ከፍተኛ መሪዎች፣ ሚኒስትሮች እና ኮሚሽነሮች ሌሎችም የተለያዩ የሥራ ኀላፊዎች የኮሚሽኑን የአራት ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት አዳምጠዉ ሃሳብ እና አስተያየት መስጠታቸውን ከኢፌዴሪ የሕዝን ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleትዕይንት ለዋጭ ቴክኖሎጂዎች
Next article“በመስኖ ልማት በሄክታር እስከ 38 ኩንታል ማምረት ተችሏል” ግብርና ቢሮ