ትዕይንት ለዋጭ ቴክኖሎጂዎች

46

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የዕይታ ልውጠት (ቪ.ኤፍ.ኤክስ እና ሲ.ጂ.አይ) በፊልም ኢንዳስትሪው ውስጥ ትርጉም ያለው እና አስደማሚ ሚናን እየተጫወቱ ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ናቸው፡፡ አሁን ላይ በፊልም ኢንዳስትሪው ተመርተው የምናያቸው አብዛኞቹ ፊልሞች በእነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ታሽተው እና ተውበው ለእይታ የሚቀርቡ ናቸው፡፡

በተለይ ደግሞ ምናባዊ እይታ የሚበዛባቸው የሳይንስ ልብወለድ፣ በድርጊት የተሞሉ አስፈሪ እና ጀብደኛ ዘውግ ያላቸው ፊልሞች ያለ እይታ ልውጠት (ቪ.ኤፍ.ኤክስ እና ሲ.ጂ.አይ) ለማሰብ ሁሉ ሊከብዱ ይችላሉ፡፡ በእነዚህ የፊልም ዘውጎች የምንመለከታቸው ምናባዊ ትዕይንቶች በሙሉ የሁለቱ ውጤቶች ናቸው፡፡

የእይታ ልውጠት (ቪ.ኤፍ.ኤክስ እና ሲ.ጂ.አይ) አብረው የሚሄዱ የፊልም ዓለም ዋልታ እና ማገር ቢኾኑም ልዩነቶች ግን አሏቸው። የእይታ ልውጠት ማለት በኮምፒውተር በመታገዝ በአንድ በተፈጠረ ምሥል ላይ ለውጦችን የሚጨምር ቴክኖሎጂ ሲኾን ሲ.ጂ. አይ ደግሞ ምዕናባዊ ምሥሎችን ሙሉ በሙሉ በኮምፒውተር በመታገዝ የመፍጠር ሂደት ነው።

ሲ.ጂ.አይ ያልተፈጠረን ወይም ያልነበረን ምስል ነገር ግን በፊልም ዳይሬክተሩ አዕምሮ ውስጥ ያለን ዓለም እንድናይ የሚረዳ ነው። ብዙ ጊዜ በእይታ ልውጠት ስር ሲ .ጂ .አይ ለየት ብሎ የሚገለጸው የሌሉ ምስሎችን በመፍጠር ነው። ሲ. ጂ. አይ በገሃዱ ዓለም የሌሉ እና ሊኖሩ ማይችሉ ነገሮችን ለመፍጠር እንጠቀምበታለን። ሁለቱም በፊልሙ ዓለም ላይ እውነት የሚመስሉ ምሥሎችን ለመፍጠር ያገለግላሉ።

በፊልም ዝግጅት ወይም ቅንብር ሂደት ውስጥ አስደማሚ ይዘቶችን ለመጨመር፣ ምናባዊ አካባቢን ለመፍጠር እና በቦታው ኾኖ ቀረፃ ለመፈጸም አስቸጋሪ የኾኑ አካባቢዎች እና ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ይህን ችግር ለመቅረፍ እና ልዩ ልውጠቶችን ለመፍጠር በመተግበሪያዎች በመታገዝ ባለሙያዎች እንዲሰሩ ይደረጋል፡፡

ከዚያም ከምናብ ያለፈ እውነት የሚመስሉ አካባቢዎች፣ ሰዎች፣ ፍጡራን እና ለሚሰራው ፊልም ማዳበሪያነት የሚያገለግሉ ትዕይንቶች ይፈጠሩበታል፡፡ ሲ.ጂ.አይን በመጠቀም የፊልም ባለሙያዎች አዲስ ምሥል፣ አዲስ ዓለምን፣ አዲስ ፍጡር፣ የሌሉ ያልነበሩ ነገሮችን ሲፈጠርልን በቀረፃ የያዝነውን ምሥል በኮምፒውተር ከተፈጠረ ምሥል ጋር በማዋሃድ እውን፣ ውህድ የሆነ እና የተሻለ ምናብ መከሰት የሚችል ትዕይንትን እንድናገኝ የሚያስችለን ደግሞ የእይታ ልውጠት ነው።

ፈጠራው ትክክለኛ የኾነ ትዕይንት እያየን እንደኾነ እንዲሰማን አድርጎ የሚያቀርብልን ቴክኖሎጂ ነው። ሁለቱ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች በፊልሙ ዓለም እጅግ ወሳኝ የሚባል ሚናን እየተጫወቱ ይገኛል። ይህ እውን እንዲኾን የሚሠሩት ደግሞ የእይታ ልውጠት ባለሙያዎች ናቸው፡፡ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ያልተሟላ የፊልም ትዕይንት ላይ ነፍስ ይዘሩበታል፡፡

የእይታ ልውጠት እና ሲ.ጂ.አይን አዘጋጅቶ በፊልም ቅንብር ውስጥ ለማካተት በሚወስደው ረጅም ጊዜ እና ብዙ ጉልበት ምክንያት በዋጋ በጣም ውድ ነው፡፡ በአንድ ነጠላ የቀረፃ ክፍል ላይ ይኽን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ ቀናትን ይወስዳል። በዚህም ምክንያት በብዙ ፊልሞች ላይ ከፊልም ሠሪዎች ቁጥር በላይ የእይታ ልውጠት እና ሲ.ጂ.አይ ባለሙያዎች ቁጥር ይበልጣል።

ሲ.ጂ.አይ እና የእይታ ልውጠት ለመፍጠር አዶቤ አፍተር ኢፌክት፣ ማክሰን ሲኒማ 4ዲ፣ አውቶ ዴስክ ማያ፣ 3D ማክስ እና ሌሎችም መተግበሪያዎች አገልግሎት ላይ ይውላሉ። እነዚህን መተግበሪያዎች በመጠቀም ነው የእይታ ልውጠት አርቲስቶች ወይም ባለሙያዎች ለእውነት የቀረቡ የፊልም ትዕይንትን እንድናይ የሚያስችሉን።

በዘርፍ ከፍሎ ለማየት ሲባል የእይታ ልውጠትን በብዙ ዓይነቶች ተከፋፍሎ እናገኘዋለን፡፡ በሚያካትታቸው ይዘቶች ብዛትም አቃፊ ቃል ኾኖ በጥቅል ሲገለጽ ሲ.ጂ.አይንም በእይታ ልውጠት ውስጥ የሚገኝ አንድ ክፍል ኾኖ እናገኘዋለን። ነገር ግን ከላይ ለማቅረብ እንደተሞከረው የእይታ ልውጠት በተቀረጸ ምስል እና በሲ.ጂ.አይ በተፈጠረ ምስል መካከል የዕይታ ልዩነት እንደሌለ አድርገን ማየት እንድንችል የሚያግዘን ነው፡፡

እነዚህ በፊልሙ ዓለም ላይ አገልግሎታቸው የገነነው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከፊልም ኢንዱስትሪው ባለፈ ሌሎች ዘርፎች ላይም በርካታ ጥቅሞችን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ አኒሜሽኖችን፣ የማስታወቂያዎችን፣ የሺዥዋል አርት ሥራዎችን፣ የዓጽመ ቅርጽ ሞዴሎችን ለመፍጠር፣ ለሥነ ሕንፃ ዲዛይኖች፣ ለምህንድስና፣ ለቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ለቪዲዮ ጨዋታዎች እና መሰል ዘርፎች አገልግሎት ላይ ይውላል።

ምንጭ
https://studioz.com.bd/vfx-vs-cgi/

Fuel Your Pipeline Faster


https://unacademy.com/content/full-forms/vfx-full-form/

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ5 ሺህ በላይ ደንብ የተላለፉ አሽከርካሪዎች መቀጣታቸውን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትራንስፖር እና ሎጅስቲክስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
Next articleለኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስፈላጊውን የቅንጅት ሥራ በጋራ በመሥራት እንደሚያግዙ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።