
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጽሕፈት ቤቱ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ቡድን መሪ ብርሃኔ አበበ እንዳሉት ጽሕፈት ቤቱ ከሚተገብራቸው ተግባራት አንዱ የከተማዋን የትራንስፖርት ፍሰት ጤናማ ማድረግ ነው። ባለፉት ዘጠኝ ወራት በከተማ አሥተዳደሩ በተደረገው ቁጥጥር በተደጋጋሚ ጥፋት አጥፍተው የተገኙ ስድስት ሺህ የሚጠጉ አሽከርካሪዎች መቀጣታቸውን ገልጸዋል።
በኮድ ሦስት የተመዘገቡ የሕዝብ አሽከርካሪዎች፣ ከመናኻሪያ ውጭ ሲጭኑ የተገኙ፣ ማኅበር የሌላቸው የወረዳ ባጃጆች፣ ማኅበር እያላቸው መርሐ ግብር የማይዙ፣ ታፔላ የማይለጥፉ፣ የደበዘዘ ወይም የማይታይ ሰሌዳ ያላቸው፣ ከጸደቀላቸው የሥራ ሥምሪት ውጭ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ፣ ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ የተገኙ፣ ከአቅም በላይ ሲጭኑ የተገኙ እና የመሳሰሉ ሕገ-ወጥ ድርጊት ሲፈጽሙ የተገኙ አሽከርካሪዎች ላይ ነው ቅጣት የተላለፈው። ከዚህም 112 ሺህ 500 ብር ለከተማ አሥተዳደሩ ገቢ ተደርጓል ብለዋል።
ቅጣቱ ወቅታዊ ሁኔታውን ታሳቢ ያደረገ መኾኑን ያነሱት ቡድን መሪው አብዛኛው አሽከርካሪዎች እንደ ጥፋታቸው ሁኔታ በማስተማር መለቀቃቸውን ገልጸዋል። ጽሕፈት ቤቱ መልካም ሥነ ምግባር እና የአገልጋይነት መንፈስ ተላብሰው ማኅበረሰቡን እንዲያገለግሉ በየዓመቱ እስከ 5 ሺህ ለሚኾኑ አሽከርካሪዎች የተሃድሶ ሥልጠና ሲሰጥ እንደነበር ያነሱት ቡድን መሪው በዚህ ዓመት በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ሥልጠና መሥጠት አለመቻሉን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ጽሕፈት ቤቱ ከትራፊክ ፖሊስ እና ከበጎ አድራጎት ማኅበራት ጋር በመቀናጀት የቁጥጥር ሥራ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ችግሩን ለመከላከል ማኅበረሰቡ ተባባሪ እንዲኾን ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!