
- እስከ የካቲት መጨረሻ ብቻ 811 የቴሌኮም ማጭበርበርና አደጋዎች ተከስተዋል፡፡
- በ2011 ዓ.ም ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ጠፍተዋል፡፡
በአማራ ክልል የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ደኅንነትን በመጠበቅ የአገልግሎት ጥራቱን ለማሻሻል ስምምነት ተፈጽሟል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም፣ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የሰላምና ደኅንነት ቢሮ እና በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ዞኖችና ብሔረሰብ አሥተዳደሮች ናቸው ሥምምነቱን ትናንት ማምሻውን በባሕር ዳር የተፈራረሙት፡፡ በዘርፉ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ስርቆቶች እና ጉዳቶች፣ የኃይል መቆራረጥ፣ የጸጥታ ችግሮች፣ የቴሌኮምና የኃይል ማጭበርበር ችግሮች ሀገርን ለኪሳራ እየዳረጉ እንደሆነ በስምምነቱ ላይ ተገልጧል፡፡ ሥምምነቱ የመሠረተ ልማት ደኅንነቶችን ለማረጋገጥና የአገልግሎት ጥራቱ ለማሻሻል የሚያስችል ቅንጅታዊ አሠራር ለመተግበር እንደሚያግዝ ታምኖበታል፡፡ ችግሮቹ ልማቱን በማጓተት ከፍተኛ ለሆኑ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምክንያት እንደሆኑ ተመላክቷል፡፡
እንደ ተቋሙ መረጃ በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ የካቲት 2012 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ 811 የቴሌኮም ማጭበርበርና አደጋዎች ተከስተዋል፤ ከዚህ ውስጥ 128 የሚሆኑት በአማራ ክልል ውስጥ ነው የተከሰቱት፡፡
በኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘርፍ ደግሞ በአማራ ክልል ስድስት “ዲስትሪክቶች” እና 120 የአገልግሎት ማዕከላት አሉ፡፡ የኤሌክትሪክ ተደራሽነቱም 51 በመቶ ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ የኃይል መቆራረጥ ችግር እና የተደራሽነት ጥያቄዎች በዘርፉ እየቀረቡበት ነው፡፡
አገልግሎቱ በሚፈለገው ልክ ተደራሽ ካለመሆኑ ባለፈ ሆን ተብለው እና በድንገት በሚፈጸሙ ጉዳቶችና ስርቆት ምክንያት በ2011 ዓ.ም ብቻ በክልሉ ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መሠረተ ልማቶች መጥፋታቸውን በአማራ ክልል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ጣሰው ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ መሠረተ ልማቶችን መጠበቅ የቅድሚያ ሥራ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ይህ የሚሆነውም የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ጥሬ ዕቃዎቹ ውድ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ከፍተኛ ጥያቄዎች በመሆናቸውም ነው ብለዋል፡፡
መሠረተ ልማቶቹ የብዙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እስትንፋስ በመሆናቸው የየአካባቢዎቹ አስተዳደሮች በኃላፊነት መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ከዞኖችና ከብሔረሰብ አስተዳደሮች የተገኙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም በየአካባቢው ያሉ የመሠረተ ልማት ተደራሽነት እጥረቶች እንዲፈቱና የቅንጅት አሠራሩ እንዲጎለብት ጠይቀዋል፡፡ የመሠረተ ልማቶችን ደኅንነት ዜጎች ባለቤት ሆነው እንዲጠብቁት ከማድረግ ባሻገር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና ሕጋዊ አሠራሮችን ማሻሻል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋማት ኃላፊዎችም አዳዲስ የመሠረተ ልማት አጠባበቅና የአገልግሎት ማሻሻያ ቴክሎጂዎችን በመተግበር ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከየአካባቢው አስተዳደሮች ጋር በቅንጅት ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
ስምምነቱ ያለውን ሀብት በአግባቡና በጥራት መጠቀም ለማስቻልና የመልካም አስተዳደር መጓደል ጥያቄዎችን በቅንጅታዊ አሠራሮች ለመፍታት የሚያስችል እንደሆነ ታምኖበታል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ