
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች በወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ላይ ውይይት አድርገዋል። በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ከመጋቢት ወር ጀምሮ በክልሉ ሁሉም ዞኖች ተሰማርተው ለተከታታይ 20 ቀናት ያደረጉት ድጋፍ እና ክትትል ያስገኘው ውጤት በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በውይይቱ ላይ በስፋት ተነስቷል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ካደረጉት የድጋፍ እና ክትትል ስምሪቱ ተሳታፊ ከፍተኛ መሪዎች መካከል በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሐ ደሳለኝ እንደገለጹት የስምሪቱ ዋና ዓላማ በሁሉም አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ የልማት ሥራዎች በተገቢው መልኩ እንዲፈጸሙ እና ሕዝቡም ተጠቃሚ እንዲኾን ለማስቻል ነው።
የከፍተኛ መሪዎቹ የመስክ ሥምሪት በተለይም የክልሉን የፀጥታ ሁኔታ ያስተካከለ እንደነበር አቶ ፍስሐ ተናግረዋል። ታችኛውን የአመራር መዋቅር በማጠናከር እንዲሁም ሕዝቡን በማቀናጀት እና በማንቃት የሰላሙ ባለቤት ኾኖ እንዲሠራ መደረጉንም ገልጸዋል።
አቶ ፍስሐ በየዞኖቹ የተሰማሩት መሪዎች በርካታ መድረኮችን በመፍጠራቸው የሕዝቡን ስሜት እና ፍላጎት ለማዳመጥ ተችሏል ብለዋል። በመድረኮች ሕግ ይከበር፣ ሰላም ይረጋገጥ፤ የተቀላጠፈ አገልግሎት ይቅረብ እና የመሳሰሉትን ተጨባጭ ጥያቄዎች ሕዝቡ በሰከነ መንገድ ማቅረቡን እና በመንግሥት ለተከናወኑ ሥራዎችም እውቅና መስጠቱን አንስተዋል።
የድጋፍ እና ክትትል ሥራው መንግሥት እና ሕዝብን አናብቧል፤ አስተዋዩ ሕዝብ ጽንፈኛው ቡድን ከሚነዛው ፕሮፓጋንዳ በተቃራኒ በመቆም መንግሥት ለሠራቸው የልማት ሥራዎች እውቅና እና ምሥጋና አቅርቧል፤ የጎደለው እንዲሟላም ጠይቋል ነው ያሉት አቶ ፍስሐ። በቀጣይም ውስንነቶችን ለይቶ በመገምገም እና በማረም ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የሰላም፣ የመልማት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶችን ለማስተካከል እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ እንደገለጹት የከፍተኛ መሪዎቹ ስምሪት የክልሉ አሁናዊ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ እስከ ቀበሌ ድረስ ዘልቆ ለመመልከት ያስቻለ ነበር።
ነጋዴዎችን፣ አርሶ አደሮችን፣ ወጣቶችን እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማግኘት ማወያየታቸውንም አቶ ሲሳይ ገልጸዋል። “ሕዝቡ በገዛ ልጆቹ ትንኮሳ ሲበደል መክረሙን አዝኖ ነግሮናል፤ መሠራት ያለባቸው ልማቶች መስተጓጎላቸውንም ታዝበናል” ብለዋል። የተፈጠረው ግጭት የአማራ ክልል ሕዝብን የማይመጥን፣ ይልቁንም ወደኃላ የሚያስቀር እኩይ ተግባር እንደነበር ሕዝቡ አምርሮ መግለጹንም አቶ ሲሳይ አመላክተዋል።
ጥያቄዎች የሚመለሱት በጋራ በመቆም እና በመወያየት ብቻ መኾኑን ሕዝቡ ጠንቅቆ እንደሚረዳ በውይይቶች ሁሉ ጎልቶ መንጸባረቁንም ተናግረዋል። ሕዝቡ በተገኘው ሰላም ተደስቷል፤ ሕግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያለውን ጽኑ ፍላጎትም ገልጿል ብለዋል። “ሁከት እና ብጥብጥ በሚናፍቁ ኃይሎች እየተታለለ የሚደናገር ሕዝብ ሊኖር አይገባም” ያሉት አቶ ሲሳይ በቀጣይም መሰል የድጋፍ እና ክትትል ስምሪት ወስዶ ከሕዝብ ጋር ግልጽ ውይይት በማድረግ የአጥፊዎችን አካሄድ ማጋለጥ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ስምሪት የጸጥታ፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ጥንካሬ እና ውስንነት ለመለየት የሚያግዝ እንደነበር ተናግረዋል። ዶክተር ደሴ እንደገለጹት አመራሮች ሕዝቡን ፊት ለፊት በማግኘት አወያይተዋል፤ በክልሉ ውስጥ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት እንዲሁም የሕዝብ እና የመንግሥትን አጀንዳ ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት ለማዞር የሚያስችሉ ምክክሮችንም አድርገዋል።
ሕዝቡ ከጸጥታ አካላት ጎን በመቆም ሰላሙን ለማስጠበቅ በመሥራቱ አንጻራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉን ዶክተር ደሴ ጠቁመዋል። ይህም ማኅበረሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ አርሶ አደሮች የግብርና ግብዓት በወቅቱ እንዲያገኙ እና ሕዝቡ ለልማቱ መሠረት የኾነውን ግብር በወቅቱ እንዲከፍል እያስቻለ መኾኑን በመስክ ስምሪታቸው መታዘባቸውን ገልጸዋል።
ዶክተር ደሴ በተዋረድ ያሉ ሁሉም አመራሮች በአንድ ማዕከል እየተገናኙ ሲመክሩ እና እየተደጋገፋ ሲሠሩ አንድነት ይጠናከራል፤ የሕዝብ ሰላም ይረጋገጣል፤ የክልሉ የልማት ጥያቄም ይመለሳል ሲሉ አብራርተዋል። የሕዝብን የልማት ጥያቄ ለመፍታት ከአልባሌ የግጭት አዙሪት መውጣት እና ዘላቂ ሰላምን መትከል እንደሚገባም አሳስበዋል። መሰል የድጋፍ እና ክትትል ስምሪቶች ቀጣይ መኾን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!