
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ በተገልጋይ የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የዋና ሥራ አሥፈጻሚ ችሎት ተጀምሯል። ችሎቱ በአገልግሎት ወቅት የሚኖሩ ቅሬታዎችን፣ ሕዝብን የሚያንገላቱ አገልግሎት አሰጣጥ እና ቅሬታዎች እየታዩ የሚፈቱበት መኾኑ ተገልጿል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ የመሬት አሥተዳደር፣ የሥራ እና ሥልጠና እንዲሁም የከተማ ደንብ ማስከበር አገልግሎት ላይ ቅሬታ ያላቸው ተገልጋዮች ጉዳይ መታየት ተጀምሯል። በችሎቱ ቅሬታቸውን ካቀረቡ የከተማ ነዋሪዎች መካከል የክፍለ ከተማው ነዋሪ ዋሴ ዘውዱ አንዱ ናቸው። በቦታ ይዞታ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቅሬታቸውንም አቅርበዋል። እንዲህ ዓይነት ፍትሕ መሰጠቱ በደል ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። መፍትሔም ሊገኝበት እንደሚችል ተስፋቸውን ተናግረዋል።
ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢ አቶ ደሳለኝ ደረሰ ተበደልኩ የሚለው ማኅበረሰብ በግልጽ ችሎት ፊት ለፊት ቀርቦ ችግሩን ማቅረቡ በራሱ አንድ እርካታ መኾኑን ጠቅሰዋል። ለወደፊቱም ተበደልኩ የሚሉ አካላት በሕዝብ ፊት በደላቸውን እያቀረቡ እውነታው መውጣቱ ትልቅ ዋጋ አለው፤ ግልጸኝነትንም ስለሚፈጥር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ተዋበ አንለይ ችሎቱ በክፍለ ከተማው ውስጥ ያሉ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እና የሚጓተቱ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ መኾኑን ጠቅሰዋል። አገልጋይ እና ተገልጋይን ፊት ለፊት በማገናኘት የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ መኾኑንም አክለዋል።
ችሎቱ በየሳምንቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ውሳኔዎች መፈጸማቸውን የሚከታተል ቡድንም መቋቋሙን ተናግረዋል። ውሳኔዎችን ያልፈጸመ መሪ እና ባለሙያ ላይም ተጠያቂነት እንደሚሰፍን ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!