“የትምህርት ቤት ምገባ ተማሪዎችን ከትምህርት ማቋረጥ እየታደገ ነው” ተማሪዎች

50

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ድርቅ፣ የሰላም እጦት እና ሌሎች ችግሮች በተደራረቡበት በአማራ ክልል በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ርቀዋል፡፡ በተለይም ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለዕለት ጉርስ ፍለጋ በሥራ በመሠማራታቸው ከትምህርታቸው ጋር ተለያይተዋል፡፡
የአማራ ክልል በተለይም በድርቅ እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ባሉ አካባቢዎች በትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ እያካሄደ ነው፡፡ የተማሪዎች ምገባም በርካታ ተማሪዎችን ከማቋረጥ ታድጓል ነው የተባለው፡፡

ተማሪ ዋሴ ደባሽ በዌከ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው፡፡ የትምህርት ቤት ምገባ መጀመር ለተማሪው ትልቅ ነገር ይዞ መጥቷል፡፡ ምገባ ከመጀመሩ በፊት ከትምህርት ቤት ባይቀርም ችግር ፈጥሮበት ነበር፤ ምገባ ከተጀመረ ወዲህ ግን ሁሉ ነገር ሰላም ኾኖለታል፤ ከእሱ ባሻገር መቅረት የሚያበዙ ተማሪዎች በሥርዓት እየተማሩ ነው፡፡

የትምህርት ቤት ምገባው ተማሪዎች እንዳይቀሩ፣ እናት እና አባትም እንዳይቸገሩ አድርጓል፤ አሁን በምግብ እጦት ምክንያት መቅረት የለም ይላል፡፡ የምገባ ሥርዓቱ ተማሪዎች እንዳያቋርጡ ብቻ ሳይኾን በክፍል ውስጥ ነቅተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እያደረጋቸው መኾኑንም ነው የተናገረው፡፡ የተማሪዎች ምገባ እንዲቀጥል እንፈልጋለን፤ ምገባው ሲቀጠል ትምህርታችን በሚገባ ለመማር ያስችለናል ብሏል፡፡

ተማሪ ናርዶስ አምባዬ የሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ከጀመረ ጀምሮ ምገባ መጀመሩን ተናግራለች፡፡ የትምህርት ቤት ምገባ ሳይኖር ብዙ ተማሪ አይመጣም ነበር፡፡ ምገባ ሲጀመር ግን ያቋረጡትም መማር ጀመሩ፣ ምግብ ይቸግራቸው የነበሩ ተማሪዎች ለመማር ይቸገሩ ነበር፤ አሁን ግን ትምህርታቸውን ይከታተላሉ ነው ያለችው፡፡ ምገባ ሳይጀምር በነበረበት ጊዜ ግን ተማሪዎች ጠዋት ቢመጡ ስለሚርባቸው ክፍለ ጊዜው ሳያልቅ አቋርጠው ይሄዱ እንደነበረም አንስታለች፡፡ ምገባው እንዲቀጥል እንፈልጋለን ብላለች፡፡

የዌከ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር በሪሁን አቤው ምገባ ለተማሪዎች ወሳኝ ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለተማሪዎች ምገባ ማድረጉ ምን ያክል የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ አካባቢው በድርቅ የተገዳ በመኾኑ ችግር መግጠሙን ያነሱት ርእሰ መመምህሩ በተለይም በሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ተማሪዎች ያቋርጣሉ የሚል ስጋት ነበረብን፣ ምገባ በመጀመሩ ግን ስጋታችን ተቀርፏል ነው ያሉት፡፡ ጥሩ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ነንም ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ተማሪዎች በደስታ እየተማሩ ነው፤ ክፍለ ጊዜውን ሳይሸራርፉ ይማራሉ፣ ለትምህርት ጥራቱም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ 1 ሺህ 643 ተማሪዎች እንደሚመገቡ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም የምገባ ተጠቃሚ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ትራንስፖርት በሌለባቸው ትምህርት ቤቶችም የባሕላዊ ማጓጓዣዎችን በመጠቀም የምገባ ሥርዓቱ ቀጥሏል፤ ይኽ ደግሞ ማኅበረሰቡ እንዲነቃቃ አድርጓል፤ የምገባ ሥርዓቱ መስፋት እና መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡ ተማሪዎችን መጥቀም ከተፈለገ ምገባ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት፡፡

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ፍታለሽ ምህረቴ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በ64 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ እየተካሄደ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከ38 ሺህ በላይ ተማሪዎች እየተመገቡ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ ምገባው በትምህርት ቢሮው አማካኝነት እየተካሄደ መኾኑን ነው ያመላከቱት፡፡ የምገባ ሂደቱ ቀጣይነት እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡ ምገባ መጀመሩን ተከትሎ ትምህርታቸውን እያቆራረጡ ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች ቁጥርም መሻሻሉን ነው የተናገሩት፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ማስኬድ ለትምህርት ሥርዓቱ ውጤታማነት አውንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ፣ ሙሉ ጊዜያቸውን ንቁ ኾነው ትምህርታቸውን እንዲከታታሉ በማድረግ በተማሪዎች ውጤት ላይ ፋይዳው የጎላ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የተማሪዎች ምገባ ሥርዓት እየተካሄደ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት 75 ሚሊዮን ብር በመመደብ በድርቅ በተጎዱ ወረዳዎች የትምህርት ቤት ምገባ ሥርዓት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ የምገባ ሥርዓቱን ሰፋ አድርጎ ለመስጠት ሰፋ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ድርጅቶችም ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡ ከተማ አሥተዳደሮች ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በመኾን ምገባ ማካሄድ መጀመራቸውንም ተናግረዋል፡፡ ምገባ ላይ ያለው አመለካከት እያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በ454 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ እየተካሄደ መኾኑን ያነሱት ምክትል ኀላፊዋ 224 ሺህ 563 ተማሪዎች እንደሚመገቡም አስታውቀዋል፡፡ ምገባው በዋናነት እየተካሄደ የሚገኘው በመንግሥት እና በሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች አማካኝት መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት በስፋት እንደሚካሄድበትም ገልጸዋል፡፡ የምገባ ሥርዓቱ በቂ አይደለም ያሉት ምክትል ኀላፊዋ ማኅበረሰቡ የምገባ ሥርዓቱን መደገፍ አለበት ብለዋል፡፡

ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ምገባ ሲጀመር አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መመሰላቸውንም ገልጸዋል፡፡ ምገባ ያለባቸው ትምህርት ቤቶች እና ምገባ ከሌለባቸው ትምህርት ቤቶች የበለጠ ተማሪዎች እንዳሏቸውም ተናግረዋል፡፡ ከተሞችን ጨምሮ ድርቅ ባላባቸው ኾነ በሌለባቸው አካባቢዎች ምገባ የሚስፈልጋቸው ብዙ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች መኖራቸውንም አመላክተዋል፡፡ የምገባ ጉዳይ ለአንድ አካባቢ ብቻ ሳይኾን በሁሉም አካባቢዎች መጀመር ያለበት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
Next articleበባሕር ዳር ከተማ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የዋና ሥራ አስፈጻሚ ችሎት ተጀመረ፡፡