የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

45

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 30ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የምክር ቤቱ ውሳኔዎች👇
1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲኾን ረቂቁ በ29ኛዉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርቦ የፀደቀውን የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ፖሊሲ መሰረት በማድረግ ፖሊሲውን ለማስፈጸም እንዲቻል ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ በ2010 ዓ.ም ጸድቆ ሥራ ላይ የዋለው አዋጅ በትግበራ ሂደት የታዩ ክፍተቶችን በተለይም የመንግሥት ሠራተኞች አሥተዳደርን ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽነት እና ተጠያቂነት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት፤ እንዲሁም ከጊዜው ጋር የሚራመድ የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ ግብዓቶችን በማከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የሸግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ በሀገሪቱ በተለያዩ ዘመናት የተከሰቱ እና የቀጠሉ ተደራራቢ እና ሰፊ የተጎጂና የአጥፊ ወሰን ያላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ ያልጠሩ ትርክቶች እና በደሎችን ለመፍታት የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ኾኖም እነዚህ አሠራሮች በእውነት፣ በዕርቅ፣ በምሕረት እና በፍትሕ ላይ የተዋቀረ እና በግልፅ ፖሊሲ የሚመራ ሁለንተናዊ የሽግግር ፍትሕ ስልትን አካታች፣ ሰብዓዊ
መብት-ተኮር በኾነ እና በተሰናሰለ መንገድ ባለመተግበራቸው የሚፈለገውን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት አልቻሉም።

ስለኾነም የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን በተደራጀ፣ በተቀናጀ እና ውጤታማ በኾነ መልኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመምራትና ለመተግበር እንዲቻል ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ከተወያያ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

ሚያዚያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

አዲስ አበባ

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

Previous articleአንድ ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተወቅቶ ወደ አርሶ አደሩ ቤት መግባቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
Next article“የትምህርት ቤት ምገባ ተማሪዎችን ከትምህርት ማቋረጥ እየታደገ ነው” ተማሪዎች