አንድ ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተወቅቶ ወደ አርሶ አደሩ ቤት መግባቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

37

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በ2016 ዓ.ም 250 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በዘር በመሸፈን ከ9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በላይ ለመሠብሠብ ታቅዶ ሲሠራ ቆይቷል። በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት 151 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ በበጋ መስኖ ስንዴም በዘር ተሸፍኗል፡፡

በአማራ ከልል ግብርና ቢሮ የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም የመስኖ ባለሙያ ተሻለ አይናለም የበጋ መስኖ ስንዴ ሥራው ከዓመት ዓመት እያደገ የመጣ መኾኑን ተናግረዋል። በ2016 ዓ.ም 250 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ቢታቀድም በዘር የተሸፈነው 151 ሺህ 625 ሄክታር መሬት ነው ብለዋል፡፡ እስካሁንም 42 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ የበጋ መስኖ ስንዴ መሠብሠቡን ተናግረዋል።

የመስኖ ባለሙያው 1 ሺህ 241 ሄክታር መሬት በኮምባይነር የተወቃ ሲኾን ቀሪው በበሬ መወቃቱን ተናግረዋል። ከዚህም 1 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የስንዴ ምርት መገኘቱን ነው የጠቆሙት። ምርቱ እስከዚህ ወር መጨረሻ ተጠቃሎ ይገባል ያሉት ባለሙያው ቆላማ አካባቢዎች ቀድመው መሠብሠባቸውን ነው የተናገሩት።

ደጋማ እና ዘግይተው በዘር በሸፈኑ አካባቢዎች ምርት ገና ነው የሚሉት ባለሙያው አርሶ አደሮች ሰብላቸውን በወቅቱ እና በጥራት መሠብሠብ እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡ አቶ ተሻለ እንዳሉት በሥራው ላይ 459 ሺህ 650 በላይ አርሶ አደሮች የተሳተፉ ሲኾን 216 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ እና 198 ሺህ 570 ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል።

አርሶ አደሮች ግንዛቤያቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ በ2013 ዓ.ም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር እድገቱ በ10 እጥፍ መኾኑን ተናግረዋል። ቴክኖሎጂን ከመጠቀም አንጻርም አርሶ አደሮች የምርት ብክነት እንዳይፈጠር ኮምባይነር መጠቀማቸው ምርታማነትን ለማሳደግ ላለው ፍላጎት ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል። በተለይ እንደቆጋ ባሉ ኩታገጠም ማሳዎች ላይ በኮምባይነር የመሠብሠቡ ሥራ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

የድህረ ምርት ጥንቃቄን በተመለከተ ባነሱት ሃሳብ የተሻሻሉ ከረጢቶችን እና የብረት ጎተራዎችን በመጠቀም ከተባይ እና መሰል ችግሮች ምርቱን መጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የምርት ጥራትን ለማምጣት አርሶ አደሮች ወቅቱን ጠብቀው ሰብላቸውን እንዲሠበሥቡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደጀን ከተማ የታየውን አንፃራዊ ሰላም ተከትሎ የጤና መድኅን ዋስትናቸውን ዳግም ማደስ እንደቻሉ የደጀን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡