በደጀን ከተማ የታየውን አንፃራዊ ሰላም ተከትሎ የጤና መድኅን ዋስትናቸውን ዳግም ማደስ እንደቻሉ የደጀን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

26

ደብረ ማርቆስ፡ ሚያዝያ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባለፉት ሁለት ወራት ከ100 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የጤና መድኅን ዋስትናቸውን በማደስ የጤና አገልግሎት ማግኘት መጀመራቸውን የዞኑ አሥተዳደር አስታውቋል፡፡ በአማራ ክልል ለወራት በቀጠለው ግጭት ምክንያት በክልሉ የጤና ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩ ተገልጿል፡፡ በምሥራቅ ጎጀም ዞንም የፀጥታ ችግሩ በጤና ሥርዓቱ ላይ በተለይም ማኅበረሰቡ የጤና መድኅን አገልግሎት እንዳያገኝ አድርጎት ቆይቷል።

የደጀን ከተማ ነዋሪዎች አቶ ጥላሁን ታደሰ እና አሊመት እንድሪስ የፀጥታ ችግሩ የጤና ዋስትናቸውን አደጋ ውስጥ ጥሎት እንደነበር አስረድተዋል። ዛሬ ላይ ግን የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም የጤና መድኅን ዋስትናቸውን በድጋሜ አድሰዋል። ነዋሪዎቹ ከስድስት ዓመታት በፊት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አባል በመኾናቸው በዓመት አንድ ጊዜ በሚከፍሉት አነስተኛ ወጭ የቤተሰባቸውን የጤና ዋስትና ማረጋገጣቸው እፎይታን እንደፈጠረላቸውም ነግረውናል።

የደጀን ከተማ አሥተዳደር የማኅበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ቡድን መሪ ታድሏል ብርሃኑ በዞኑ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጦ ቢቆይም ከየካቲት/2016 ዓ.ም ጀምሮ አባላቱ የጤና ዋስትናቸውን በማደስ የጤና አገልገሎት እንዲያገኙ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የሥራ ሂደት መሪው የማኅበረሰቡ ግንዛቤ ማደጉን ተከትሎም የጤና መድኅን ዋስትናቸውን በራሳቸው ተነሳሽነት በማደስ በኩል የከተማ አሥተዳደሩ ነዋሪዎች የሰጡት አዎንታዊ ምላሽም አበረታች እንደኾነ አስገንዝበዋል። የደጀን ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ይርጋ በዛ በማኅበረሰብ ጤና መድኅን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በአባላቱ የሚነሱ ቅሬታዎችን በመቀነስ አገልግሎቱን ፍትሐዊ ለማድረግም ከተማ አሥተዳደሩ ከህክምና ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ብለዋል።

አቶ ይርጋ የደጀን ከተማ ነዋሪዎች እና ተቋማት አቅም የሌላቸው ወገኖች የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲኾኑ በማድረግ ላሳዩት አጋርነትም ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል። በምሥራቅ ጎጃም ዞን የታየውን አንፃራዊ ሰላም ተከትሎ ባለፉት ሁለት ወራት ከ100 ሺህ በላይ የዞኑ ነዋሪዎች የጤና ዋስትናቸውን በማደስ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መኾናቸውን ከአሥተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

ዘጋቢ፡- ዘላለም አስፋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በሁሉም ዞኖች በመሰማራት ውጤታማ የድጋፍ እና ክትትል ሥራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ገለጹ።
Next articleአንድ ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተወቅቶ ወደ አርሶ አደሩ ቤት መግባቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።