የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በሁሉም ዞኖች በመሰማራት ውጤታማ የድጋፍ እና ክትትል ሥራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ገለጹ።

57

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ ውይይት እያደረጉ ነው። በውይይቱ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን ውይይቱ ወቅታዊ የክልሉን የሰላም፣ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ሥራዎች የሚገመግም እና ቀጣይ አቅጣጫዎችንም የሚያስቀምጥ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በየደረጃው ያሉ የክልሉ አመራሮች የተሰጣቸውን ኀላፊነት ከሕዝብ ጋር በመቀናጀት ምን ያህል እየተወጡ እንደኾነ የሚዳሰስበት ውይይት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከመጋቢት ጀምሮ በሁሉም ዞኖች ስምሪት በመውሰድ እስከ ታች ዘልቀው ድጋፍ እና ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል። በዚህ ስምሪት ብዙ ሥራዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል።

በተለይም ዞኖች አካባቢ ያሉ አመራሮች ከሕዝቡ ጋር ስላላቸው ቅንጅት ግንዛቤ የተወሰደበት ነበር ብለዋል። የሕዝብ እና የመንግሥት ምልከታ እና ተግባቦት ምን እንደሚመስል በዝርዝር የተፈተሸበት፣ ችግር ያለባቸውን ቦታዎች በማወቅ ለማስተካከል ውጤታማ ስምሪት የተደረገበት እንደነበርም አመላክተዋል።
የመስክ ስምሪቱ የሕዝቡን ፍላጎት በውል በመለየት ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችል ነበርም ብለዋል።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ስምሪት ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች የሚፈታ አመራር ለመገንባት የሚያስችል ግብዓት የተገኘበት እንደነበርም አመላክተዋል። በውይይቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲኾን በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊው ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል።

ከሰላም አኳያ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውንም አመላክተዋል። በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ገልጸዋል። የሕዝብን ልማት ሲያደናቅፍ የቆየው ጽንፈኛ ቡድን ከሕዝብ መነጠሉን ጠቁመዋል። “ሕዝቡ ቁሜልሃለሁ እያለ ሲያወናብደው የከረመውን ኃይል ጥፋቱን በመገንዘብ በአደባባይ አውግዞታል” ነው ያሉት። የሕዝብን ጥያቄ የተሸከመ በመምሰል ሕዝብን ሲበድል የቆየውን ጽንፈኛ ቡድን መንግሥት እየተከታተለ በማሰስ ሕግ እያስከበረ፣ ለሕዝብም እፎይታ እየሰጠ ነው ብለዋል።

በዚህም ሕዝብ በአደባባይ ወጥቶ ለመንግሥት ያለውን ድጋፍ አሳይቷል ነው ያሉት። በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተጠናከረ የፀጥታ መዋቅር እና አመራር ተቋቁሞ የሕዝብን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት እየተሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል። ዶክተር ዘሪሁን ከልማት እና መልካም አሥተዳደር አኳያ ጥሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

ለአብነትም:-
✍️ የገቢ ግብር አሰባሰብ እንቅስቃሴን ወደተሟላ ሥራ መግባቱ፣
✍️ በግብርና ሥራዎች ላይ ርብርብ ለማድረግ ተነሳሽነት መፈጠሩ፣
✍️ የሥራ እድል ፈጠራ ግብረ ኃይል ሥራ እንዲጀምር መደረጉ
✍️ ትምህርት ባልጀመሩ አካባቢዎች ትምሕርት ቤቶች መከፈታቸው
✍️ የጤና ሥራዎች በትኩረት እየተሠሩ መኾኑን እና
✍️ ሕዝብን በማያገለግሉ ባለሙያዎች እና አመራሮች ላይ ጠንካራ የተጠያቂነት ሥራ መዘርጋቱ ከልማት እና መልካም አሥተዳደር አኳያ በጥንካሬ ተነስተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የማሳ ተደጋግሞ መታረስ ጠቀሜታው ብዙ ነው” ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር)
Next articleበደጀን ከተማ የታየውን አንፃራዊ ሰላም ተከትሎ የጤና መድኅን ዋስትናቸውን ዳግም ማደስ እንደቻሉ የደጀን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡