
ደብረ ማርቆስ: ሚያዚያ 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን የእነማይ ወረዳ በተያዘው የምርት ዘመን ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ መኾኑን አስታውቋል። አርሶ አደር ግፋ ቸሩ በምሥራቅ ጎጃም ዞን እነማይ ወረዳ የትመን ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በመስኖ ልማት ተግባር ተሰማርተው እንደቆዩ እና በዘርፉም ገቢያቸውን ማሻሻል እንደቻሉ አስረድተዋል።
አርሶ አደር ግፉ በዚህ የምርት ዘመንም የተለያዩ የአትክልት እና ፍራፍሬ ሰብሎችን አልምተዋል፡፡ በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት እንደወትሮው ሁሉ ሙሉ ጊዜያቸውን በማሳቸው ማሳለፍ አለመቻላቸውን ነግረውናል። የተፈጠረው ግጭት ለልማት እንቅፋት በመኾኑ ችግሩ እንዲፈታ አጥብቀው ይሻሉ።
ሌሎች በየትመን ቀበሌ የሚኖሩ አርሶ አደሮችም እንደ አርሶ አደር ግፉ ሁሉ የክረምት ዝናብን ከመጠበቅ በመውጣት ለዓመታት ያለ ጥቅም በቀያቸው የሚፈስሱ ወንዞች ወደ ማሳቸው እንዲፈስሱ እና እንዲያለሙ በማስቻል ዓመቱን ሙሉ አረንጓዴ የማይለየው ቀየ ፈጥረዋል። የእነማይ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ድረስ ሞሱ በነባር እና በአዲስ ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ ቢኾንም በክልሉ የተከሰተው ግጭት በወረዳው የግብርና እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል።
የእነማይ ወረዳ የአርሶ አደሮችን የመስኖ ልማት እንቅስቃሴ የተመለከቱት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ የፀጥታ ችግሩ እንቅፋት ቢኾንም አርሶ አደሮቹ በመስኖ ልማት እንቅስቃሴው ያሳዩትን ትጋት አድንቀዋል። ዋና አሥተዳዳሪው ለመኸር እርሻ ዝግጀት የግብርና ግብዓት ወደ አርሶ አደሮች እንዳይደርስ የሚሠሩ ኃይሎች ከእኩይ ድርጊታቸው እንዲታረሙም አሳስበዋል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2015/2016 የምርት ዘመን በግጭት ምክንያት የታጣውን ምርት ለማካካስ ከሕግ ማስከበር በተጓዳኝ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አሥተዳደሩ አስታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
