
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2016/17 የመኸር እርሻ ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማረስ 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል፡፡ በዚህም አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዙር እርሻ መታረሱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
አርሶ አደር አለሙ ወሌ በዳንግላ ወረዳ የውንብሪ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከሦስት ሄክታር መሬታቸው ውስጥ ሁለት ሄክታሩን አርሰውታል፡፡ አርሶ አደር አለሙ ማሳቸውን እንደሚዘሩት ሰብል ዓይነት ለይተው ያርሳሉ፡፡ በዚህም ምርታቸው ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ አርሶ አደር አለሙ ወቅቱን ጠብቆ ማረስ በምርታቸው ላይ ለውጥ ማምጣቱንም ተናግረዋል፡፡ የግብርና ምክረ ሃሳብ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉም ይገልጻሉ፡፡
አርሶ አደር አለሙ እንዳሉት መሬታቸውን እንደሚዘሩት የሰብል ዓይነት የእርሻ ድግግሞሹ እንደሚለያይ ያነሳሉ፡፡ ደጋግመው እንደሚያርሱም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመትም አንድ ሄክታር መሬት በቆሎ አንድ ሄክታር መሬት ደግሞ ጤፍ እና ዳጉሳ ቀሪውን መሬታቸውን ሌሎች ሰብሎችን ከፋፍለው ለመዝራት አቅደዋል፡፡ ለበቆሎ የሚኾን ማዳበሪያም ቤታቸው ማስገባታቸውን አንስተዋል፡፡ አርሶ አደር አለሙ በአካባቢያቸው በተሠጣቸው ኀላፊነት መሠረት ጓደኞቻቸውም ደጋግመው እንዲያርሱ ምክር እንደሚሠጡም ይገልጻሉ፡፡
ማሳ ሲለሰልስ ምርት ይጨምራል፡፡ ያላረሰ አርሶ አደር በተባይ እና በአረም ሲሰቃይ እንደሚከርም ያነሱት አርሶ አደሩ መሬት ያበቀለው ሰብል ከልቡ እንዲያፈራ አርሶ አደሮች ማሳቸውን ደጋግመው ማረስ አለባቸው ብለዋል፡፡ “ስንፍና ቀለብ አይኾንም” የሚሉት አርሶ አደር አለሙ በእጃችን ያለውን ነገር መሥራት ከእኛ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) በ2016/17 የመኸር እርሻ ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማረስ 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ 2 ሚሊዮን 216 ሺህ 748 ሄክታ መሬት በአንደኛ ዙር፣ 1 ሚሊዮን 261 ሺህ 381 ሄክታር መሬት በሁለተኛ ዙር፣ 267 ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ በሦስተኛ ዙር እርሻ መታረሱንም አንስተዋል፡፡በአጠቃላይ ከእቅዱ አንጻር 39 ነጥብ 9 በመቶ መሸፈን መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
የእርሻ ድግግሞሽ በርካታ ጥቅም እንዳለው ያነሱት ዳይሬክተሩ ማሳዎች ተደጋግመው በታረሱ ቁጥር በአፈር ውስጥ ተደብቀው ከወቅት ወቅት የሚሸጋገሩ ተባዮችን ለፀሐይ በማጋለጥ ተባዮችን በቀላሉ በመከላከል ተጨማሪ ምርት ለማግኘት ይረዳል ብለዋል፡፡ ማሳ ደጋግሞ ሲታረስ አፈሩ ሲብላላ ምርታማነት እንደሚጨምርም ዶክተር ማንደፍሮ አንስተዋል ፡፡ የአፈር መገለባበጥ ሰብሉ ያለችግር እንዲበቅል እና እንዲያፈራ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ሰብሎች እንደዝርያቸው የተለያየ ሥር አላቸው የሚሉት ዳይሬክተሩ ሥራቸው ርቆ መሄድ የማይችሉ ሰብሎች በቂ ንጥረ ነገር እንዲያገኙ ማሳው ተደጋግሞ መታረስ አለበት ብለዋል፡፡ የጥራጥሬ እህሎች ሥራቸው አፈርን ወደ ለምነት የመቀየር ተፈጥሮአዊ ፀጋ አላቸው፤ እንደነዚህ ዓይነት ሰብሎች ሁለት እና ሦስት ጊዜ አንድ ማሳላ ተደጋግመው ቢዘሩ ውጤት ሊያመጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ማንደፍሮ እንዳሉት አርሶ አደሮች እርሻን ደጋግሞ ማረስ በሕይወት ተሞክሮአቸው እየተለማመዱት የመጡ ቢኾንም አንዳንድ ሰዎች እንዳይዘናጉ በንቅናቄ መድረክ እና በኤክስቴንሽን እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ እርሻ ወቅትን ጠብቆ መታረስ አለበት የሚሉት ዳይሬክተሩ ሦስት እና አራት ጊዜ አረስኩ ለማለት በተከታታይ ጊዜ ማረስ አግባብ እንዳልኾነም ተናግረዋል፡፡ ይህ ላልተፈለገ ችግር ስለሚያጋልጥ የመኸር እርሻ በሚጀመርበት ወር ቀድሞ ማረስ ተገቢ መኾኑን አብራርተዋል፡፡
አርሶ አደሮች ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ ምርታማነታቸውን በማሳደግ ሀገራዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪ ግብዓትን በምክረ ሃሳቡ መሰረት መጠቀም፣ ዘርን በወቅቱ መዝራት፣ አረምን እና ተባይን መከላከል እና ሌሎችን በጥምር ማስኬድ እንደሚገባ ምክራቸውን አክለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
