
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቤት ከታች ነውና ገመናን ይሸፍናል፣ መከፋትን ይደብቃል፤ መራብ እና መጠማትን አያሣጣም። ንጽሕናቸው እምብዛም የኾኑ ልቦሶች በችግር የተጎዱ ልቦችን ደብቀዋል፣ የተራቡ ሆዶችን፣ የተጠሙ ጉሮሮዎችን ሸፍነዋል። ቤት የከለላቸው ችግሮች፣ ሀዘኖች፣ ጦም ውሎ ጦም ማደሮች ሞልተዋል።
ምን ይሉኝ የያዛቸው፣ ከሰው ፊት መቅረብ ያሳፈራቸው፣ ክብርን ከማጣት መራብ መጠማት ይሻላል ብለው በችግር ውስጥ የሚኖሩም አይታጡም። ብዙዎች ከአቅማቸው በላይ በኾነው የኑሮ ውድነት ይብከነከናሉ፤ ለልጆቻችን ምን እናጉርስ፣ ምንስ እናልብስ የሚሉ እናቶች አሉ። ወጪው ከገቢው እየላቀ፣ ፍላጎቱ ከሚገኘው ጋር አልጣጣም እያለ ብዙዎችን አስቸግሯል።
በልቶ ማደር ቅንጦት የኾነባቸውም መልተዋል። “ገበያውን አይራበው፣ ገበያው ጥጋብ ይሁን” እያለ የሚመኘው የሀገሬው ሰው በገበያ ያገኘውን እንደአሻው ሸምቶ መምጣት አልችል ብሏል። አንድም ገበያው ይራባል። ሁለትም ዋጋው አልቀመስ ይላል። የኑሮ ውድነት ይሉት የዘመኑ ፈተና ብዙዎችን እንደጦር ሰቅዞ ይዟቸዋል።
ነዋሪነታቸው ባሕርዳር ከተማ ነው። ጣና ክፍለ ከተማ ቀበሌ 13 በሚባለው ሠፈር ይኖራሉ። ስማቸው እንዲወጣ አልፈለጉም። የልጆች እናት ናቸው። ልጆቻቸው በእርሳቸው ሃሳብ ያድራሉ። ሲያገኙ ያጎርሷቸዋል። ሲያጡ በእናት አንጀታቸው ደባብሰው፣ ነገ የተሻለ ቀን እንደሚኾን ነግረው ያስተኟቸዋል። “ኑሮ ዳገት ነው” ይሉታል። አቅመ ደካማ የማይወጣው አስቸጋሪ ዳገት። በተመቻቸላቸው የሴፍቲኔት (የምግብ ዋስትና) ሥራ እየሠሩ እንደኾነ ነግረውኛል። ነገር ግን ሠርተው የሚያገኙት ገቢ እና የኑሮ ውድነቱ አልጣጣም ብሏቸዋል።
“ሴፍትኔት እየሠራሁ ነው። ነገር ግን ሰርቼ የማገኘው ገንዘብ ቤተሰቤን አያሥተዳድርም። በቁርጡ የቀን ሥራ ይሻለኝ ነበር። ግን የቀን ሥራም ቢኾን የለም፡፡ ምንም እየበቃኝ አይደለም። “ችግረኛ ነው የኾንኩት” ነው ያሉኝ። የምግብ ወጪ ሲታሰብ፣ የቤት ኪራይ አለ። እኛ ኗሪዎች ሳንኾን አኗኗሪዎች ነን ይላሉ። በጣም ከባድ ኑሮ ነው እየኖርን ያለነው ብለውኛል።
በተለይም በአማራ ክልል የተፈጠረው የፀጥታ ችግር አስቸጋሪ እንደነበር ነው ያስታወሱት። የግጭቱን ጊዜ ተው አታንሳው ይላሉ። የምንበላው ሁሉ እስከማጣት ደርሰን ነበር፤ ደረቆት እየቆላሁ ሰዎች ያላቸውን ምግብ እየሰጡን ነው እየበላን የሰነበትን ብለውኛል። ሻል ያሉ ዘመዶች እና ወዳጆች ባይኖሩኝ ኖሮ አስቸጋሪ ነበር ነው ያሉኝ። ለእኛ ፍቱን መድኃኒት ሀገር ሰላም ሲሆን እና ደህና ሥራ መሥራት ስንችል ነውም ብለውኛል። የኑሮ ውድነት እንኳን ለእኛ ለድሃዎች ከእኛ ለተሻሉትም አስቸጋሪ ነው ይላሉ።
“ጥቂት ስትገኝ ገቢያ ሄደን የተገኘችውን ገዝተን መምጣት ነው” ነው ያሉኝ። በልቶ የሚያድርም ሳይበላ የሚያድርም አለ፣ በተለይ ለእኛ በችግር ውስጥ ላለነው ሰላም ነው የሚያስፈልገን ብለዋል። “ሽንኩርት፣ ቲማቲም አንጠይቅም፣ ማሽላይቱን፣ ዳጉሳይቱን ጠይቀን ገዝተን ማስፈጨት ነው፣ ለእኛ ቤት ወጥ ሽንኩርት ቅንጦት ነው፣ ድሀ ሽንኩርት ምን ያደርግለታል፣ ሽሮ ካገኘ በቃው” ይላሉ ችግራቸውን ሲናገሩ።
ሰላም እና ሥራ ማግኘት የእኛ መዳኛችን ነው፣ ከዚያ ውጭ ግን የምንጎርሰውም የምናጎርሰውም እናጣለን ነው ያሉት። ሰላም ከኾነ ቢያንስ ሠርተን እንበላለን፣ ለውጡ ይቅርብን፣ ሠርተን እንብላ ነው ያሉኝ። “ልጆች ላሏት እናት ከድህነት ላይ የኑሮ ውድነት ተጨምሮ አስቸጋሪ ነው” ይላሉ።
ታዲያ ብዙዎችን ያማረረው የኑሮ ውድነት መፍትሔ ምን ይኾን?
በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህር ይስማው አየልኝ (ዶ.ር) በኢትዮጵያ በተለይም የምግብ ነክ እና የዕለት ከዕለት ፍጆታዎች ላይ ከፍተኛ የኾነ የዋጋ ንረት አለ ይላሉ። የኑሮ ውድነቱን የጨመረው የዋጋ ንረቱ ነው። ይሄም ከፍተኛ ገቢ የሌላቸውን እና በቅጥር ገቢ የሚተዳደሩ ወገኖችን በከፍተኛ ኹኔታ ይጎዳል ነው ያሉት። የዋጋ ንረት የመግዛት አቅምን ያሽመደምዳል ነው የሚሉት። የመግዛት አቅም ሲቀንስ ደግሞ ኑሮ ይከብዳል።
በሀገር ላይ የሚነሱ ግጭቶች የኑሮ ውድነትን ያባብሳሉ ነው የሚሉት። ለአጠቃላይ ማኅበራዊ እድገት ሰላም ወሳኙ ጉዳይ መኾኑን ነው ያመላከቱት። ግጭት እና የሰላም እጦት በምጣኔ ሃብት ላይ ከፍተኛ የኾነ ጉዳት ያስከትላልና። በኢትዮጵያ ሚሊኒዬም ከተከበረበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የኾነ የዋጋ ንረት መኖሩን ያነሱት መምህሩ የምግብ ነክ የዋጋ ንረት ደግሞ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ነው የገለጹት። መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች አብዛኛውን ገቢያቸውን የሚያውሉት ለምግብ ፍጆታ ነው፤ ይሄም አቅማቸውን በማውረድ እና በመናድ ኑሮውን አክብዶታል ነው የሚሉት። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖች አቅማቸው ሳይሻሻል በመካከለኛ ገቢ የሚገኙ ወገኖች በዋጋ ንረት ምክንያት አቅማቸው ከወረደ ሌላ ችግር ያስከትላል ነው ያሉት።
መካከለኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች ያሉባት ሀገር የእድገት ደረጃቸው ከፍ ይላል የሚሉት መምህሩ የመካከለኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች ለለውጥ መነሻዎች ናቸው፤ የኑሮ ውድነት የመካከለኛ ገቢ ያላቸውን ወገኖች ወደ ዝቅተኛ አወረዳቸው ማለት ቤተሰቦቻቸው መጎዳት ብቻ ሳይኾን አጠቃላይ በምጣኔ ሃብቱ ላይም ጉዳት ያድርሳል ብለዋል።
ብዙ ጊዜ የኑሮ ውድነት ሲበረታ ሕዝብ በፖሊሲ እንዲስተካከል ይጠይቃል፣ ሕዝብ ሲጠይቅ መንግሥት ማሻሻያዎችን ተጠቅሞ ያሻሽላል፣ ነገር ግን ፈታኝ ነው ይላሉ። ምክንያቱም አንዳንዶቹ ጉዳዮች ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ ሊኾኑ ይችላሉ ብለዋል። ምክንያቱም አንዳንድ የኑሮ ውድነት ምክንያቶች ዓለም አቀፍ ተጽዕኖዎች ሊኾኑ ስለሚችሉ ነው። ያም ቢኾን መንግሥት ኑሮን የሚያሻሽልበት አቅሙም፣ መሳሪያውም አለው ነው የሚሉት።
የኑሮ ውድነት ላይ የማሻሻያ መፍትሔዎች ሲታጡ ለግጭቶች መነሻ ምክንያት ሊኾኑ እንደሚችሉ የሚያመላክቱት መምህሩ ግጭት ግን የኑሮ ውድነትን አይፈታም ብለዋል። የኑሮ ውድነት ግጭት ይቀሰቅሳል፣ ነገር ግን ግጭቱ ግን ለኑሮ ውድነቱ መፍትሔ አያመጣም፣ የተሻለው መንገድ መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመኾን እያሻሻለ እንዲሄድ ማድረግ ነው ይላሉ። ማሻሻያዎችን ማድረግ ግጭትን እንደሚቀንስ ነው የተናገሩት።
መንግሥት የመሪነት ሚናውን በመጫዎት፣ ሕዝብን በማስተባበር፣ ለአንድ የጋራ ዓላማ እንዲነሳ በማድረግ የኑሮ ውድነትን ማሻሻል ይሻላል፣ ሕዝብ ደግሞ ምርት እና ምርታማነትን በመጨመር የኑሮ ውድነትን መዋጋት የሚችልበት እድል አለው ነው ያሉት። መንግሥት የመሪነት ሚናውን ሲወጣ ሕዝብ ደግሞ ምርት ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት፣ ግብርና በሚገባ ካላመረተ የኑሮ ውድነት መጨመሩ አይቀርም ብለዋል።
ለመገመት ከሚያዳግት በላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረትን እና የኑሮ ውድነትን መቀልበስ የቻሉ ሀገራት መኖራቸውን ነው መምህሩ የተናገሩት፡፡ መምህሩ ከቻሉት ሀገራት ይቻላል የሚለውን ተሞክሮ መውሰድ ይገባልም ብለዋል፡፡ ነገር ግን የወሰዱትን የመፍትሔ እርምጃ ከእኛ ሀገር ላይ አምጥቶ መተግበር አይገባም፤ በሌሎች ሀገራት የተወሰደው የመፍትሔ እርምጃ በእኛ ሀገር ላይ ላይሠራ ይችላልና ነው ያሉት። ችግሮችን ለመፍታት የሚወሰዱ እርምጃዎች የሀገራቱን ኹኔታ ያገናዘበ መኾን አለበት። ኢትዮጵያውያንን የኑሮ ውድነት የፈተናቸው አስቀድሞም ኑሯቸው አቅመ ደካማ ስለነበር ነው ይላሉ። ፈቃደኝነት እና ቁርጠኝነት ካለ ግን የኑሮ ውድነቱን ተጽዕኖ መቀነስ እና ማሻሻል ይቻላልም ብለዋል።
የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ንረትን ከፈቱ ሀገራት ግን ይቻላል የሚለውን ተሞክሮ መውሰድ መልካሙ ነገር መኾኑንም አመላክተዋል። የኑሮ ውድነት የሚያስከትለውን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ከመተንተን ይልቅ መፍትሔው ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል። ሁሉም የሚጠበቅበትን በማድረግ ለመፍትሔው መሥራት እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጠውን ማንሳት፣ አሉታዊ አካሄዶችን ብቻ መተንተን መፍትሔ እንደማይኾኑ ነው ያመላከቱት።
ምርታማነትን በማሳደግ አቅርቦትን እና ፍላጎትን ማጣጣም ይገባልም ብለዋል መምህሩ። መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ የመፍትሔ እርምጃዎች መኖራቸውን የተናገሩት መምህሩ እየተወሰዱ ያሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እና የመፍትሔ እርምጃዎች በጊዜ ሂደት ለውጥ የሚያመጡ እንጂ ለውጣቸው በእለት የሚታዩ አለመኾናቸውን ነው የተናገሩት። ለሚመጣው ለውጥ መታገስ እና መተጋገዝ ይገባል ብለዋል። ለአብነት ብሔራዊ ባንክ የመፍትሔ እርምጃዎችን እየወሰደ መኾኑንም ገልጸዋል። ከሚወሰዱ መፍትሔዎች በተጓዳኝ የሚፈታተን የገበያ ሥርዓት መኖሩንም አንስተዋል። ለተጨባጭ ለውጥ በጋራ መሥራት እና መታገስ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል። የኑሮ ውድነትን ማሻሻል የጋራ ጥቅም መኾኑንም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
