
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ጎንደር ኮማንድፖስት ከምዕራብ ጎንደር ሁሉም ወረዳዎች ከተውጣጡ የፀጥታ አካላት ጋር በወቅታዊ የቀጣናው ሰላም እና ፀጥታ ላይ ያተኮረ ውይይት በገንደውኃ ከተማ ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ጎንደር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ እና የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ የአማራ ክልልን ከፅንፈኛው እና ዘራፊው ቡድን ነፃ ለማድረግ በሁሉም አካባቢ ኦፕሬሽኖችን በማድረግ የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ብለዋል።
ሠራዊቱ ከክልሉ የፀጥታ ኃይል ጋር በመቀናጀት ባደረጋቸው ዘመቻዎች የቀጣናው ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ መምጣቱንም አንስተዋል፡፡
የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ በድንበር አካባቢ የሚታዩትን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ኮንትሮባንድ እና ፀረ ሰላም ኃይሎችን ለመቆጣጠር ሕዝቡን ያሳተፈ የቅንጅት ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል። የምዕራብ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ ቢክስ ወርቄ የዞኑን ሰላም እና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ ሕዝቡን ያሳተፈ ሥራ በመሠራት ላይ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ነፍጥ አንግበው ወደጫካ ለገቡ ታጣቂዎች በተደረገ የሰላም ጥሪ በዞኑ ከ400 በላይ ታጣቂዎች የሠላም ጥሪውን ተቀብለው ከሕዝቡ ጋር መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።
አሥተዳዳሪው እንዳሉት ዞኑን ከጽንፈኛው ኃይል ነፃ ለማድረግ የፀጥታ ኃይሉ ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እንዲሠራ የማድረግ፣ ቀጣናው ከድንበር ጋር ተያያዥነት ያለው በመኾኑ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን የመቆጣጠር ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
