
ከሚሴ: ሚያዚያ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በባቲ ከተማና አከባቢው የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር በትኩረት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጿል። የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በምሥራቅ አማራ ከሚገኙ የዞን እና የከተማ አሥተዳደር የጤና ባለሙያዎች ጋር በማኅበረሰቡ የጤና ችግሮች ዙሪያ በኮምቦልቻ ከተማ ምክክር አካሂዷል። ምክክሩ በክልሉ ብሎም በአካባቢው በተጋረጡ የጤና ስጋቶች እና የጤና ችግሮች ሲከሰቱ ጉዳት ሳያደርሱ መፍትሔ ማበጀት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ነበር። በውይይቱ ከተነሱ የጤና ስጋቶች ውስጥ ኮሌራ ዋነኛው ነው።
በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባቲ ከተማ እና በዙሪያው የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን እና 83 ሰዎች ሕመሙ እንዳለባቸው መታወቁን በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የደሴ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር አንተነህ ደመላሽ ገልጸዋል። በአካባቢው በሕመሙ የተያዙ ሰዎች እንዲለዩ እና እንዲታከሙ ብሎም ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት የተጠናከረ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም አቶ አንተነህ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ውይይቱ ቅንጅታዊ አሠራርን ለመፍጠር ያለመ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ተባብሮ እና ተቀናጅቶ መሥራት ከተቻለ የተከሰተውን ወረርሽኝ በቀላሉ መቆጣጠር እንደሚቻልም ተናግረዋል። ወረርሽኙን በፍጥነት ለመከላከል እና በቀጣይነትም የማኅበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ ኢንስቲትዩቱ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት የታየበት ማንኛውም ሰው ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ ምልክቱን የሚያሳይ ሰው ሲያጋጥምም ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንደሚገባ ኀላፊው አሳስበዋል። አቶ በላይ ሁሉም የእጅን እና የአካባቢን ንጽህና በመጠበቅ፣ ውኃን አክሞ በመጠቀም እንዲሁም ንጽህናው የተጠበቀ ምግብ በመመገብ ኅብረተሰቡን ከኮሌራ ወረርሽኝ እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- መስዑድ ጀማል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
