የአካባቢን ሰላም ለማጽናት ኅብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የወልድያ ከተማ አሥተዳደር አሳሰበ።

17

ወልድያ: ሚያዝያ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከተማ አሥተዳደሩ በቦርድ ከሚተዳደሩ ተቋማት ሠራተኞች ጋር ውይይት አድርጓል። የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋዬ ገብሬ ከሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ጋር በተደጋጋሚ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ዛሬም በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በቦርድ ከሚተዳደሩ ተቋማት ሠራተኞች ጋር መምከር አስፈላጊ በመኾኑ መድረኩ መዘጋጀቱን አንስተዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ሊፈታ የሚችለው በሰላማዊ መንገድ ሊኾን እንደሚገባም መግባባት ላይ መደረሱን ነው የገለጹት። የወልድያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ከተማ አሥተዳደሩ በደፈረሰ ሰላም ውስጥም ኾኖ በርካታ የልማት ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል።

ነገር ግን የሚዲያ እና የልማት ሥራን ለሕዝብ የማስተዋወቅ ሥራ ይቀረናል ነው ያሉት። በውይይት መድረኩ ላይ የኑሮ ውድነት እና የሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች መነሳታቸውን አውስተዋል። የኑሮ ውድነትን ለማቅለል ከተማ አሥተዳደሩ ሸማች ማኅበራት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ሕዝብ ምርት እንዲያቀርቡ በገንዘብ እየደገፈ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በየግቢው የግብርና ምርት ማምረት የሚያስችል የከተማ ግብርናን ለማስፋፋትም አሥተዳደራቸው እየሠራ መኾኑን ከንቲባው ተናግረዋል። ከሰላም እና ፀጥታ አኳያ መንግሥት፣ ሕዝብ እና የመንግሥት ሠራተኞች የድርሻቸውን በመወጣት የአካባቢያቸውን ሰላም ለማጽናት መግባባት ላይ መድረሳቸውን አቶ ዱባለ ገልጸዋል። ሰላምን ለማጽናት ኅብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ነው ከተማ አሥተዳደሩ ያሳሰበው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለክልላዊ እና ብሔራዊ ፈተናዎች ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውን ተማሪዎች ገለጹ።
Next articleበባቲ ከተማና አከባቢው የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር በትኩረት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።