
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለክልላዊ እና ብሔራዊ ፈተናዎች ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መኾኑን የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታውቋል። የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ፈተና ዝግጅትን አስመልክቶ የንቅናቄ መድረክ አዘጋጅቷል። ንቅናቄው የተካሄደው “በራሱ የሚሠራ ትውልድ ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ነው” በሚል መሪ መልዕክት ነው። መምሪያው ተማሪዎች በክልላዊ እና ብሔራዊ ፈተናዎች ውጤታማ እንዲኾኑ እየሠራ መኾኑን አመላክቷል። ውጤታማ የሚያደርጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን እና ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጿል።
በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የጎርደማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪው አማረ ገበየሁ ለፈተና ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መኾኑን ተናግሯል። መምህራን ለፈተናው የሚያግዙ ሥራዎችን በመሥራት እገዛ እያደረጉላቸው መኾኑንም ገልጿል። ለፈተናው በቡድን የማጥናት ልምድ እንዳላቸውም ተናግሯል። “የሰላሙን ሁኔታ ማስጠበቅ ለፈተናው ዝግጁ እንድንኾን ያደርጋል” ብሏል።
ተማሪ ቤተልሔም ወለላው መምህራን በሚያደርጉላቸው እገዛ መሠረት ለፈተናው እየተዘጋጁ መኾናቸውን ተናግራለች። ከእነርሱ በፊት የ8ኛ ክፍል ፈተና የተፈተኑ ተማሪዎችን በመጠየቅ ለፈተናው ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጻለች። መምህራን ቅዳሜ እና እሑድ ሁሉ እየጠሩ እያስተማሯቸው መኾናቸውን ተናግራለች። የከበዳቸውን ክፍል እንደሚከልሱላቸው እና በተገቢው መንገድ እንደሚያስረዷቸው ነው የገለጸችው። የቤተ መጻሕፍት እና የመጻሕፍት ችግር እንዳለባቸውም ተናግራለች።
የአጼ ሠርጸ ድንግል መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ዓባይነህ የሽዋስ ተማሪዎችን ለማብቃት ከተማሪዎች እና ከመምህራን ጋር በመግባባት እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። ተማሪዎችን ለማብቃት ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል። በቀጣይ ከወላጆች እና ከሌሎች የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር በመኾን ተማሪዎችን ለውጤት ለማብቃት እንሠራለን ነው ያሉት። ያልተሸፈኑ የትምህርት ይዘቶች እንዲሸፈኑ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። በከተማዋ ሰላም በመኖሩ የትምህርት መቆራረጥ አለመኖሩንም ተናግረዋል።
የባሕርዳር መሰናዶ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ታረቀኝ ዓለሙ በየትምህርት አይነቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ብቁ ማድረግ የሚችሉ መምህራን መመደባቸውን ተናግረዋል። ክፍለ ጊዜ እንዳይባክን፣ የባከነ ክፍለ ጊዜ ካለም እንዲካካስ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። ቅዳሜ እና እሑድን እንዲሁም የተቃራኒ ፈረቃዎችን በመጠቀም ያልተሸፈኑ ይዘቶች እንዲሸፈኑ እያደረጉ መኾናቸውን ገልጸዋል። አብዛኛው የትምህርት ይዘት በመጠናቀቅ ላይ መኾኑንም ተናግረዋል።
ይዘት ከመሸፈን ባለፈ ተማሪዎች በመረጧቸው መምህራን አማካኝነት ተጨማሪ ትምህርቶች እየተሰጡ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ውጤታማ የኾኑ እና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለማፍራት ሥራቸውን በተገቢው መንገድ እንደሚከውኑም አስታውቀዋል። የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ኃይለማርያም እሸቴ ክልላዊ እና ብሔራዊ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። መደበኛ የትምህርት ክፍለጊዜውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እየተደገ መኾኑንም ገልጸዋል። እሑድ እና ቅዳሜን ጨምሮ ተማሪዎች የቤተመጻሕፍት አገልግሎት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።
ተማሪዎች እስከመጨረሻው ጊዜ ለፈተናው ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። ትምህርት መምሪያው በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች የሚደረጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አጠናከሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። ከባለፈው ዓመት የተሻለ የመጻሕፍት አቅርቦት መኖሩን የተናገሩት ኀላፊው የደረሱትን መጻሕፍት በፍጥነት ለተማሪዎች ማድረሳቸውንም ገልጸዋል። መጽሐፍትን ለእያንዳንዱ ማዳረስ ግን አለመቻሉን ተናግረዋል። የመጻሕፍት አቅርቦቱ በቂ አይደለም፣ ነገር ግን ባለው ማዘጋጀት ተገቢ ስለኾነ የዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
የማጣቃሻ መጻሕፍት በስፋት እንዲገዙ ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል። መምህራንም በቅንነት ተማሪዎችን እያዘጋጁ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ተማሪዎች የሥነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። ክልላዊ እና ብሔራዊ ፈተና ሲባል የሚኖረውን መደናገጥ በመቅረፍ ተረጋግቶ መዘጋጀት እና ፈተናውን በአግባቡ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። በእርጋታ መሥራት ከቻሉ ከመላ ሀገሪቱ ተማሪዎች ጋር ተወዳድረው ወደ ሚፈልጉት ማለፍ እንደሚችሉም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ ከሰሞኑ ለአሚኮ በሰጡት ማብራሪያ የ6ኛ ክፍል እና የ8ኛ ክፍል ተፈታች ተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ መኾኑንም ገልጸዋል። ብሔራዊ እና ክልላዊ ፈተናዎች በሁለት ዙሮች እንደሚሰጥም ተናግረዋል። ቀድመው የተመዘገቡት እና ትምህርታቸውን በአግባቡ የተከታተሉ ሰኔ/2016 ዓ.ም እንደሚፈተኑም አስታውቀዋል። ዘግይተው የተመዘገቡ፣ በመካከል ያቆራረጡ እና መማር ያለባቸውን ትምህርት በአግባቡ ያልተማሩ ተማሪዎች በሁለተኛ ዙር ይፈተናሉ ነው ያሉት።
ተማሪዎች በየትኛው ዙር መፈተን እንደሚፈልጉ ለመወሰን ከተማሪዎች እና ከተማሪ ወላጆች ጋር ውይይት እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ወቅቱ ፈታኝ ቢኾንም የትውልድ ግንባታ የማይቋረጥ በመኾኑ ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። ተማሪዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርት እና ለፈተና ዝግጅት እንዲያውሉም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
