
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን በተሰጠው ኀላፊነት ለ6 ወር ያህል በተለያዩ በማኅበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ላይ ሪፖርት ማዘጋጀቱን ምክትል ዳይሬክተሩ ዮናታን ተስፋዬ ተናግረዋል።
ፌስቡክ፣ ዩቲዩብ፣ ኤክስ ወይም የቀድሞው ትዊተር እና ቴሌግራም ሪፖርቱ የተዘጋጀባቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ናቸው። የሕዝብ አስተያየት፣ ቅሬታ እና ጥቆማ የመረጃ ምንጮች መኾናቸው ተጠቁሟል። አግላይነት በይዘት ስርጭቱ ውስጥ በስፋት የተስተዋለ መኾኑን በሪፖርቱ ተገልጿል።የጥቅል ፍረጃ የሚንጸባረቅባቸው መኾናቸውም ተነስቷል።
በሕዝብ መካከል መለያየትን በመፍጠር፣ ለጥቃት የሚያነሳሱ እንዲኹም ለእርስ በእርስ ግጭቶች የሚያጋልጡ ምልክቶች የሚታዩበት መኾኑንም በሪፖርቱ ተጠቅሷል። የጥላቻ ንግግር ደረጃ ከፍተኛ እና አስጊ መኾኑን፣ ችግሩ አሁንም ተባብሶ መቀጠሉን እና አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
እንደ ሪፖርቱ ገለጻ የጥላቻ ንግግር በኅብረተሰብ ውስጥ ወደ አደገኛ መከፋፈል እያመራ መኾኑ ተስተውሏል። ከችግሩ መባባስ አንጻር የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ለሚታዩ የጥላቻ እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ትኩረት አለማድረጋቸውም ተጠቅሷል። ኢቢሲ እንደዘገበው ድርጅቶቹ በጥቅሉ ሪፖርት ከተደረገላቸው የጥላቻ ንግግር ውስጥ 2 በመቶውን ብቻ ከዕይታ ማገዳቸው ተገልጿል። ድርጅቶቹ የማኅበረሰቡን ደንብና መመሪያ አክብረው ኀላፊነታቸውን እና ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ተብሏል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
